የሰዎች ደኅንነት ማረጋገጥ ቀዳሚው የመንግሥት ግዴታ ነው – ኢሰመኮ

በመተከል በንፁሃን ላይ የደረሰውን ጥቃት ባለመከላከልም ሆነ በሌላ መልኩ ጥቃቱን የፈጸሙና ያባባሱ ሰዎችን ሕግ ፊት የማቅረብ ሂደት እንዲጀመር የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽን አሳሰበ።

 “የሰዎች ደኅንነት ማረጋገጥ ቀዳሚው የመንግሥት ግዴታ ነው ” በሚል በመተከል ዞን፣ ቡለን ወረዳ፣ በኩጂ ቀበሌ በንፁሃን ላይ የደረሰውን ጥቃት አስመልክቶ የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን  መግለጫ አውጥቷል።

ኮሚሽኑ በመግለጫው በክልሉ ያለው የሰብአዊ መብቶች ጥበቃ በከፍተኛ ሁኔታ እተዳከመ መሄዱን በመግለጽ፤ የጥቃቱን ሂደት በተመለከተ ከሚመለከታቸው አካላት እና ከተጎጂዎች ጋር በመነጋገር ሲከታተልና ሲያጣራ መቆየቱን አስታውቋል።

ኮሚሽኑ ሁኔታውን እስካጣራበት ጊዜ ድረስ በቡለን ሆስፒታል 36 ተጎጂዎች እርዳታእየተደረገላቸው ሲሆን አብዛኞዎቹ በጥይት ሌሎቹ በቀስት የቆሰሉ መሆናቸውን አረጋግጧል በኩጂ ቀበሌ በሰው ሕይወት እና አካል ላይ ከደረሰው ጉዳት በተጨማሪ የደረሱ ሰብሎችና የተሰበሰቡ ማሳዎች በእሳት መጋየታቸውም ጭምር መረጃ እንደደረሰው ገልጿል።

በድባጤ ወረዳ ዶንበን ቀበሌ ስጋት የገባቸው ነዋሪዎች ከታኅሣሥ 14 ቀን 2013 ዓ.ም. ጀምሮ ቀዬአቸውን ጥለው እየተሰደዱ እንደሆነም ኮሚሽኑ መረጃ አለኝ ብሏል በመግለጫው።

በቤኒሻንጉል ጉሙዝ የሚከሰቱ ጥቃቶችን ተደጋጋሚነትና የክልሉን ሰብአዊ መብቶች ጥበቃ ሁኔታ አስመልክቶ፣ የፌዴራሉንና የክልሉን መንግሥታት የተጠናከረ ትብብርና ከፍተኛ ትኩረት እንደሚሻ  ኢሰመኮ ሲያሳስብ የቆየ ቢሆንም ጥቃቶቹ በመልክ እና በስፋት እየተባባሱ መምጣታቸው  ነው የተገለጸው።

በጥቃቱ ጉዳት ለደረሰባቸውን እና ለተፈናቀሉ ሰዎች የህክምና እና ሰብአዊ እርዳታ እንዲቀርብ እንዲሁም ተገቢው ማጣራትና ጥቃቱን ባለመከላከልም ሆነ በሌላ መልኩ ጥቃቱን የፈጸሙና ያባባሱ ሰዎችን ሕግ ፊት የማቅረብ ሂደት ከወዲሁ እንዲጀመርም ኮሚሽኑ  አሳስቧል።

በአካባቢው የሚገኘውን የፀጥታ ኃይልና መዋቅር የሰዎችን ደኅንነት ሙሉ በሙሉ ለማረጋገጥ በሚያስችል መልኩ በከፍተኛ ደረጃ በአፋጣኝ እንዲጠናከርም ኢሰመኮ ጥሪ አቅርቧል።