የሱዳኑ ጠ/ሚኒስትር “የቀውስ ጊዜ ኮሚቴ” አቋቋሙ

ጠቅላይ ሚኒስትር አብደላ ሐምዶክ

ጥቅምት 9/2014 (ዋልታ) ጠቅላይ ሚኒስትር አብደላ ሐምዶክ በሱዳን ለተከሰተው ፖለቲካዊ ቀውስ መፍትሄ ለመፈለግ የሚያስችል “የቀውስ ጊዜ ኮሚቴ” ማቋቋማቸው ተነገረ።

ኦማር ሐሰን አል ባሽር ከሁለት ዓመት በፊት ከሥልጣን ከተወገዱ በኋላ ጠቅላይ ሚኒስትሩ አገሪቱን የገጠማት “በጣም አደገኛ” ፖለቲካዊ ቀውስ ነው ያሉትን ችግር ለመፍታት ነው ቡድኑን ያዋቀሩት ሲል የአገሪቱ ዜና ወኪል ሱና ዘግቧል።

ትናንት ሰኞ ካርቱም ውስጥ በተካሄደው አስቸኳይ የካቢኔ ሚኒስትሮች ስብሰባ ላይ ነው የቀውስ ጊዜ ኮሚቴ ማቋቋማቸውን ጠቅላይ ሚኒስትር ሐምዶክ ያስታወቁት።

ሱዳን ለገጠማት ከባድ ፖለቲካዊ ቀውስ መፍትሄ ለማፈላለግና የተጀመረውን የሽግግር ሂደት ለማሳካት በተዋቀረው ኮሚቴ ውስጥ የተቃዋሚ ፓርቲ ተወካዮችም መካተታቸው ተገልጿል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ አገሪቱን ወደ ዲሞክራሲያዊ ሥርዓት ለማሸጋገር የሚደረገውን ጥረት ወደኋላ የመመለስ ስጋትን ፈጥሯል ያሉትን ለሳምንታት የዘለቀ ፖለቲካዊ ውጥረትን ለማርገብ ሁሉም ችግሩን ከሚያባብሱ እርምጃዎች ተቆጥበው ውይይት እንዲደረግ ጥሪ አቅርበዋል።

ሐምዶክ ይህንን ያሉት በአገሪቱ ፖለቲካ ውስጥ ጠንካራ ተጽእኖ ባለው የአገሪቱ ጦር ሠራዊት የተደገፈና የሽግግር አስተዳደሩ እንዲወገድና ጦሩ አገሪቱን እንዲመራ የሚጠይቁ ሰልፍ በፖሊስ መበተኑን ተክትሎ ነው።

ባለፈው ቅዳሜ የጀመረው የተቃዋሚዎቹ ሰልፍ በርካታ የጦር ኃይሉ ደጋፊ የሆኑ ሱዳናውያን የተሳተፉበት ሲሆን፣ በፕሬዝዳንቱ ጽህፈት ቤት አካባቢ በመሰባሰብ ጦር ሠራዊቱ ሥልጣን እንዲጨብጥ ጥሪ አድርገው ነበር።

ከኦማር አልበሽር ከሥልጣን መወገድ በኋላ በአሁኑ ጊዜ ሱዳን በሲቪልና በወታደሮች ጥምረት በተመሰረተ ሉአላዊ ምክር ቤት አማካይነት በሽግግር መንግሥት እየተመራች ትገኛለች።