የሱዳን ምሁራንና ሙያተኞች መንግስታቸው በግድቡ ዙሪያ የሚያራምደው አቋም የተሳሳተ መሆኑን እየገለፁ ነው – አምባሳደር ይበልጣል አዕምሮ

አምባሳደር ይበልጣል አዕምሮ

ሚያዝያ 06/2013 (ዋልታ) – የሱዳን ምሁራንና ሙያተኞች የህዳሴው ግድብ ለአገራቸው የሚያስገኘውን ጥቅም ስለሚገነዘቡ መንግሥታቸው የሚያራምደው አቋም የተሳሳተ መሆኑን እየገለጹ መሆናቸውን በሱዳን የኢትዮጵያ ባለሙሉ ስልጣን አምባሳደር ይበልጣል አዕምሮ ገለጹ።

አምባሳደሩ የግድቡ ፋይዳና ጠቀሜታ ለሱዳን እጅግ በጣም ሰፊ መሆኑን ገልጸው፣ ይህን የተረዱ አንዳንድ የሱዳን ምሁራን እንደሚሉት የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ማለት ለግብጾች የአስዋን ግድብ የሆነውን ያህል እንደሆነና ይህም ግብጾች ከአስዋን ግድብ የሚያገኙትን አይነት ጥቅም ሱዳናውያን ከህዳሴው ግድብ ያገኛሉ ብለዋል።

የሱዳን መንግስት በህዳሴው ግድብ ላይ ያለውን የተሳሳተ አቋም በተመለከተ ሱዳናውያን በተለይ የሱዳን ጋዜጠኞች በስፋት የሚቃወሙትና የሚተቹት ነው የሚሉት አምባሳደሩ፤ በግድቡ ዙሪያ ያለው የሱዳን አቋም የፖለቲከኞች እንጂ የሕዝብ ፍላጎት አይደለም ብለዋል።

እንደ አምባሳደር ይበልጣል ገለጻ፤ ሕዝቡ የግድቡን ጥቅም አጥብቆ ይረዳል፤ ይፈልጋል፤ ምንም እንኳን የተዛቡ መረጃዎችን በመስጠት አጠቃላይ የ20 ሚሊየን ሕዝብ ህልውና አደጋ ላይ ሊወድቅ ነው፤ እየተባለ በስፋት የሚሰራጭ መረጃ ቢኖርም ሕዝቡ ግን ስለ ግድቡ ጥቅም ከአሁን በፊት ሲነገረው የነበረውን ያውቃል።

አንዳንድ ባለሙያዎችና ጋዜጠኞች የራሳቸውን ኃላፊዎች በተለይ የውሃ ሚኒስትሮቻቸውን እስከመተቸት ይደርሳሉ ያሉት አምባሳደር ይበልጣል፣ ትናንት ስለ ግድቡ ጥቅም በጎነት ስትናገሩን አልነበር? ዛሬ ምን ተፈጠረና ነው ስለግድቡ ጉዳትና ጥፋት የምትገልፁልን እያሉ እየጠየቁ ነው ማለታቸውን ከኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።