የሱዳን ጠቅላይ ሚኒስትር ሥልጣን ሊለቁ ነው

ታኅሣሥ 13/2014 (ዋልታ) የሽግግር መንግሥቱን ስምምነት እየጣሰ ባለው ወታደራዊ ክንፉ ጫና እያደረባቸው ያሉት የሱዳኑ ጠቅላይ ሚኒስትር አብደላ ሃምዶክ ሥልጣን ለመልቀቅ እንዳሰቡ ተገለፀ።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሥልጣን የመልቀቅ ሐሳባቸውን ለፖለቲከኞች ቡድን መናገራቸውን ሮይተርስ ለሃምዶክ ቅርብ ከሆኑ ሁለት ምንጮች መስማቱን አስነብቧል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ባለፈው ጥቅምት በሌተናል ጄነራል አብዱል ፈታህ አል ቡርሃን በሚመራው ጦር መፈንቅለ መንግሥት ተደርጎባቸው ለቁም እስር ከተዳረጉ በኋላ በተደረገ የስምምነት ከሳምንታት በፊት ወደ ሥልጣናቸው መመለሳቸው የሚታወስ ነው።
ሮይተርስ ምንጮቹን ጠቅሶ እንደዘገበው ከሆነ ሃምዶክ በሥልጣን ላይ እንዲቆዩ ለማሳመን ቢሞከርም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ውሳኔያቸውን እንደማይቀይሩ አረጋግጠዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር አብደላ የሽግግር መንግሥቱ ሲመሰረትም ሆነ ከሳምንታት በፊት የተደረገው ስምምነት ተግባራዊ የማይሆን ከሆነ ሥልጣኔን እለቃለሁ ማለታቸውን ይታወሳል፡፡
የሽግግር መንግሥቱ ሲመሰረት በነበረው ስምምነት መሰረት የወታደራዊ ክንፉ ባለፈው ኅዳር ሥልጣን ማስረከብና አገሪቱ በሲቪሉ ክንፍ የበላይነት እየተመራች ለምርጫ ራሷን ማዘጋጀት ይገባት ነበር።
ሆኖም አሁንም ወታደራዊ ክንፉ ፈላጭ ቆራጭ ሆኖ ለመዝለቅ እየሰራ መሆኑ ሱዳናዊያን የአደባባይ ተቃውሞን የበለጠ እንዲገፉበት እያደረጋቸው አገሪቱ ወደባሰ የፖለቲካ ቀውስ ውስጥ ገብታለች።