የሲዳማ ክልል ለአገር መከላከያ ሠራዊት የ105 ሚሊየን ብር ድጋፍ አበረከተ

ኅዳር 20/2014 (ዋልታ) የሲዳማ ክልል ለአገር መከላከያ ሠራዊት 80 ሚሊየን የገንዘብ እና የ25 ሚሊየን ብር የአይነት በአጠቃላይ የ105 ሚሊየን ብር ድጋፍ አበርክቷል።

የአሸባሪው የሕወሓት ኃይል ኢትዮጵያን ለማፍረስ ያለመው ህልሙ ቅዠት ሆኖ ቀርቷል ያሉት የክልሉ ርዕሰ መስተዳደር ደስታ ሌዳሞ አሸባሪ ቡድኑ ወደ ኋላ እየፈረጠጠ ያለው በአንድነት በመቆማችን ነው ብለዋል።

እኔ እያለሁ ሀገር አትፈርስም በማለት ራሳቸው ወደ ግንባር በመዝመት ምሳሌ የሆኑ ጠቅላይ ሚኒስትሩን ተከትለን ሁላችንም ይህን የሽብር ቡድን እስከወዲያኛው ለመቅበር ልንዘምት ይገባል ብለዋል፡፡

ርዕሰ መስተዳደሩ ጦርነቱ ፈርጀ ብዙ በመሆኑ የሚችል ግንባር በመዝመት ሌላው ደግሞ በተሠማራበት የስራ መስክ በትጋት በመስራት ለሀገሪቱ ኢኮኖሚ እድገት ሊረባረብ እንደሚገባ አሳስበዋል።

የሲዳማ ክልል ለአገር መከላከያ ሰራዊት እና ፀጥታ ኃይሉ የተለያዩ ድጋፎችን በማድረግ  አጋርነቱን እያሳየ መሆኑን የገለጹት ርዕሰ መስተዳድሩ በቀጣይም ድጋፉን አጠናክሮ እንደሚቀጥል ተናግረዋል።