የሲዳማ ክልል ምስረታ በዓል ካለምንም የፀጥታ ችግር በሰላም እንዲጠናቀቅ አስተዋጽኦ ላበረከቱ አካላት ምስጋና ቀረበ

የካቲት 17/2013 (ዋልታ) – የሲዳማ ክልል ይፋዊ የምስረታ በዓል ካለምንም የጸጥታ ችግር በሰላም እንዲጠናቀቅ አስተዋጽኦ ላበረከቱ አካላት የክልሉ መንግስት ምስጋና አቀረበ።

የክልሉ የመንግስት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ ሃላፊ አቶ ፍልጶስ ናሆም ትናንት ማምሻውን በሰጡት መግለጫ በሀዋሳ ከተማ በደመቀ ሁኔታ የተከበረው የክልሉ ምስረታ በዓል ያለምንም የፀጥታ ችግር በሰላም ተጠናቋል።

በዓሉ በሰላም እንዲጠናቀቅ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ላበረከቱ የሀገር ሽማግሌዎች፣ አባገዳዎች፣ ወጣቶች እንዲሁም በየደረጃው ለሚገኙ የክልሉና የከተማ አስተዳደሩ የፀጥታ አካላት ምስጋና አቅርበዋል።

በተለይ እንግዶችን በኢትዮጵያዊ ጨዋነት በመቀበልና በማስተናገድ ከፍተኛ መስዋዕትነት ለከፈለው ለሲዳማ ክልል ነዋሪዎች የክልሉ መንግስት ከፍተኛ ምስጋናና አክብሮት እንዳለው አስታውቀዋል።

ደስታችንን ለመካፈል በአካል ለተገኛችሁ የፌዴራል፣ ክልል መንግስታት፣ዲፕሎማቶች፣የህዝብ ተወካዮችና ሌሎችም ልዑካን ምስግናችን ለማቅረብ እንወዳለን ብለዋል።

የደቡብና ኦሮሚያ አጎራባች ዞኖች ህዝቦችና አመራሮች ላሳዩት ቀና አበርክቶ ክልሉ ያለውን ምስጋና ያቀርባል ብለዋል አቶ ፍልጶስ በመግለጫቸው።

የሲዳማ ህዝብ በከፍተኛ መስዋዕትነት ያገኘውን ክልል ድል ከመላው ኢትዮጵያዊያን ጋር በጋራ ለማክበር በሚዘጋጅበት ወቅት የህዝብ ሠላምና አንድነት የማይዋጥላቸው አካላት በተደበቁበት በማህበራዊ ትስስር ገፆች ያልተገባ ነገር ሲያሰራጩ የነበሩ አካላትን ህዝቡ በነቅስ በመውጣትና ምስረታውን በማክበር እንዳሳፈራቸውም አስታውቀዋል።

እንደ ኢዜአ ዘገባ እነኚህ አካላት ከዚህ ቀደም ለዶክተር አብይ አህመድ የክልሉ ነዋሪዎች ያላቸውን ድጋፍ በሰላማዊ ሰልፍ ለመግለጽ እንዳይወጡ የተለያዩ ዘመቻዎች ቢያደርጉም ህዝቡ እንዳልሰማቸው ማረጋገጣቸውን ገልጸዋል፡፡

በክልል ይፋዊ ምስረታ የታየው ኢትዮጵያዊ አንድነትን በማጠናከር ለጋራ ሃገራዊ ልማትና ብልጽግና በጋራ መቆም እንደሚገባ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡

በክልል ምስረታው በዓል ወቅት የታየውን የተቀናጀ የፀጥታ ስራ በልማት ለማረጋገጥ ህብረተሰቡ ከመንግስት ጎን እንዲሰለፍም ጥሪ አቅርበዋል።