የሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ኤርጎጌ ተስፋዬ (ዶ/ር) የስራ ርክክብ አደረጉ

መስከረም 28/2014 (ዋልታ) በአዲሱ የመንግስት ምስረታ የሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳይ  ሚኒስትር ሆነው የተሾሙት ኤርጎጌ ተስፋዬ(ዶ/ር)  ከቀድሞ የሴቶች፣ ሕፃናትና ወጣቶች ሚኒስትር ፊልሰን አብዱላሂ ጋር የስራ ርክክብ አድርገዋል፡፡

አዲስ ለተሾሙት ሚኒስትርም ወይዘሮ ፊልሰን አብዱላሂ እና የመሥሪያ ቤቱ ከፍተኛ የሥራ አመራሮች አቀባበል አድርገውላቸዋል፡፡

ለሚኒስትሯ ስለ ሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር አደረጃጀትና እየተሰሩ ስላሉ ስራዎች እንዲሁም ወደፊት የታቀዱ ዕቅዶች በተለይም የተቋሙን የ10 ዓመት የሴክተር የልማት ዕቅድና አዳዲስ ሃሳቦችን ላይ የቀድሞ የሴቶች፣ ሕፃናትና ወጣቶች ሚኒስቴር ሚኒስትር ፊልሰን አብዱላሂ ገለፃ ማድረጋቸው ተመላክቷል፡፡

ኤርጎጌ ተስፋዬ(ዶ/ር) በቀጣይ እንደ ሀገር በርካታ ስራዎችን መስራት ስለሚጠበቅብን ተቋማዊ አደረጃጀቱንና አሠራሩን ማጠናከር፣ የአመራሩን የመፈጸምና የማስፈጸም አቅም ማሳደግ፣ ሲንከባለሉ የመጡ ጎታች አመለካከቶችን በግንዛቤና በንቅናቄ መፍጠሪያ ተግባራት መዋጋትና ማቃናት እንዲሁም ነባር የህግ ማዕቀፎችን ሳይሸራረፉ ተግባራዊ እንዲሆኑ ማድረግና በጥናት ተመስርቶ አዳዲስ ማዕቀፎችን ማውጣት ይጠበቅብናል ብለዋል፡፡

በመጨረሻም ለተደረገላቸው አቀባበል አመስግነዉ ከሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ አመራርና ሰራተኛ ጋር በመወያየት በቅንጅት ስራዎችን እንደሚሰሩ መግለፃቸውን ከ የሴቶች፣ ሕፃናትና ወጣቶች ሚኒስቴር  ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡