የሴቶች ቀን በእቴጌ መነን የልጃገረዶች አዳሪ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተከበረ

የካቲት 29/2014 (ዋልታ) “የፆታ እኩልነትን ዛሬ ማስፈን ለተሻለ እና ቀጣይነት ላለው ነገአችን” በሚል መሪ ሀሳብ የሴቶች ቀን በኢትዮ ቴሌኮም አዘጋጅነት በእቴጌ መነን የልጃገረዶች አዳሪ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተከበረ፡፡
የኢትዮ ቴሌኮም ዋና ሥራ አስፈፃሚ ፍሬህይወት ታምሩ ሴት ልጅ በርትታ በሁሉም መስክ ከሰራች ስኬታማነቷ የላቀ መሆኑን ገልጸው በተለይም ተማሪዎች የነገ አገር ተረካቢ በመሆናቸው ያሰቡትን አላማ ለማሳካት ከወዲሁ መበርታት ያስፈልጋል ብለዋል፡፡ ለዚህም የሴቶች ሁሉን ዐቀፍ ተሳትፎ ሊጎለብት እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡
የሴቶች ተሳትፎ ለማሳደግ ኢትዮ ቴሌኮም በትምህርት ቤቱ ከፍተኛ ውጤት ላስመዘገቡ 10 ተማሪዎች የታብሌት ሽልማት እና ለ480 ሴት ተማሪዎች ለአንድ ዓመት የሚሆን የንፅህና መጠበቂያ ድጋፍ አድርጓል፡፡
በተለይም ሴት ተማሪዎች ለአገር፣ ለወገን፣ ለቤተሰብ የሚጠቅሙ ጠንካራ እና ብርቱ ለመሆን መትጋት እንደሚገባ ያነሱት ዋና ሥራ አስፈፃሚዋ ለሴቶች እድል አለመስጠት እና ተሳትፏቸውን አለማጉላታችን ከፍተኛ ክፍተት ሲፈጥር እንደቆየና ይህንን ለማስተካከል ከፍተኛ የሴቶች ብርታት እንደሚያስፈልግ አንስተዋል፡፡
ዓለም ዐቀፍ የሴቶች ቀን በኢትዮጵያ ለ46ኛ ጊዜ በዓለም ዐቀፍ ደረጃ ደግሞ ለ111ኛ ጊዜ በዛሬው ዕለት እየተከበረ ይገኛል፡፡
በአመለወርቅ መኳንንት