መስከረም 18/2015 (ዋልታ) በኢትዮጵያ አስተናጋጅነት በሚካሄደው የምስራቅና መካከለኛው አፍሪካ የእግር ኳስ ማህበራት ምክር ቤት (ሴካፋ) ከ17 ዓመት በታች የእግር ኳስ የሚሳተፉ አገራት አዲስ አበባ መግባት ጀምረዋል።
ውድድሩ ከመስከረም 21 ቀን 2015 ዓ.ም ጀምሮ በአበበ ቢቂላ ስታዲየም የሚካሄድ ሲሆን በሁለት ምድብ ኢትዮጵያን ጨምሮ አስር አገራት ይሳተፋሉ ተብሏል።
በውድድሩ ላይ ከሚሳተፉ አገራት መካከል የብሩንዲ፣ የደቡብ ሱዳንና ሶማሊያ ከ17 ዓመት ብሔራዊ ቡድኖች ትናንት ማምሻውን አዲስ አበባ መግባታቸውን የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን አስታውቋል።
በሴካፋ የእግር ኳስ ውድድር በምድብ አንድ በአሰልጣኝ ታዲዮስ ተክሉ የሚመራው ብሔራዊ ቡድን ከታንዛንያ፣ ኤርትራ፣ ሶማሊያና ደቡብ ሱዳን ጋር ተደልድሏል።
ዩጋንዳ፣ ሩንዳ፣ ጅቡቲ፣ ሱዳንና ብሩንዲ በምድብ ሁለት የተደለደሉ አገራት መሆናቸውም ተመላክቷል።
ሆኖም ከተሳታፊ አገራት መካከል ኤርትራ እና ሩዋንዳ ከበጀት ጋር በተያያዘ ችግር ምክንያት ከውድድሩ ራሳቸውን ማግለላቸውን ፌዴሬሽኑን ጠቅሶ ኢዜአ ዘግቧል፡፡
የኢትዮጵያ ከ17 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድን ለውድድሩ 23 ተጫዋቾችን በመያዝ ከጳጉሜ 2014 ዓ.ም አንስቶ ሐያት በሚገኘው የካፍ የልህቀት ማዕከል ልምምዱን እያደረገ ነው።
የሴካፋው ውድድር እስከ ጥቅምት 9 ቀን 2015 ዓ.ም የሚካሄድ ሲሆን በውድድሩ አንደኛና ሁለተኛ የሚወጡት ብሔራዊ ቡድኖች የሴካፋ ዞንን ወክለው በአልጄሪያ በጥር ወር 2015 ዓ.ም በሚካሄደው የአፍሪካ ከ17 ዓመት በታች የእግር ኳስ ሻምፒዮና ይሳተፋሉ ተብሏል።
ለፈጣን መረጃዎች፦
ፌስቡክ https://bit.ly/3Ma7QTW