የሴካፋ የወንዶች እግር ኳስ ጫወታ በባህር ዳር ተጀመረ

ሐምሌ 10/2013 (ዋልታ) – የምስራቅና መከካለኛው አፍሪካ ሀገራት ከ23 ዓመት በታች የወንዶች እግር ኳስ ጫወታ በባህርዳር ዓለም አቀፍ ስታዲየም ተጀመረ።

በመክፈቻው ስነ- ስርዓት የባህልና ቱሪዝም ሚኒስትር ዶክተር ሂሩት ካሳው ባደረጉት ንግግር፤  ስፖርት ለህዝቦች የእርስ በእርስ ትስስር፣ ለኢኮኖሚ ግንባታና ለጤና የጎላ ሚና አለው ብለዋል።

አፍሪካውያን ለዘርፉ ትኩረት ሰጥተው በመስራት ዘርፉ የሚያበረክተውን አስተዋጽኦ በአግባቡ መጠቀም እንደሚገባም አመልክተዋል።

ውድድሩ በሦስት ምድብ ተከፍሎ በዘጠኝ የምስራቅና የመከካለኛው አፍሪካ ሀገራት ተሳታፊ የሚሆኑበት ነው።

በውድድሩዐ በምድብ አንድ  ዩጋንዳ፣ ታንዛንያና ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ፤ በምድብ ሁለት  ኢትዮጵያ፣ ኤርትራና ብሩንዲ፤ በምድብ ሶስት  ኬኒያ፣ ደቡብ ሱዳንና ጅቡቲ የተደለደሉ ሲሆን ውድድሩም ለሁለት ሳምንት እንደሚቆይ ታውቋል።

የውድድሩ መክፈቻ  በኢትዮጵያና  ኤርትራ ብሄራዊ ቡድኖች በሚያደርጉት ጨዋታ  ተጀምሯል።

በመክፈቻው ስነ-ስርዓት የኢትዮጵያ ስፖርት ኮሚሽነር አቶ ኤሊያስ ሽኩር፣ የኢትዮጰያ እግር ኳስ ፌደሬሽን ፕሬዚዳንት አቶ ኢሳያስ ጂራ ጨምሮ ሌሎችም  የፌደራልና የክልል ከፍተኛ ሃላፊዎች መገኘታቸውን ኢዜአ  ዘግቧል።