ሰኔ 29/2014(ዋልታ) የስራ እና ክህሎት ሚኒስትሯ ሙፈሪሃት ካሚል ከዓለም ዐቀፉ የስደተኞች ድርጅት የምስራቅ አፍሪካ ዳይሬክተር ሙሀመድ አብዲከር ጋር ተወያዩ፡፡
ሚኒስትሯ ከጊዜ ወደ ጊዜ አሳሳቢነቱ እየጨመረ በመጣው ቀጣናዊና ሀጉራዊ በሆኑ የሠራተኞች ፍልሰት ጉዳዮች ላይ ፣ በቀጠናው የክህሎት ልማት እና የወጣቶች የሥራ ዕድለ ፈጠራን፣ የሰራተኞች ተዘዋውሮ የመስራት፣ የዜጎችን ሰብዓዊ እና ማህበራዊ መብቶችን ማስጠበቅን በተመለከተ መወያየታቸውን አስታውቀዋል፡፡
ኢትዮጵያ በቀጠናው የሰራተኞች ፍልሰት ጉዳይ የሚኒስትሮች ፎረምን የምትመራ ሀገር እንደመሆኗ ድርጅቱ ድጋፉን አጠናክሮ ስለሚቀጥልበት ሁኔታም መምከራቸውን ከትስስር ገጻቸው ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡
ከቀጠናው ባለፈ ከሌሎች ሀገራት እና አህጉራት ጋር ህጋዊ የሆነ የሰለጠነና በከፊል የሰለጠነ የሰው ኃይል ዝውውር ሥርዓት መዘርጋት እና በትብብር ለመስራት በሚደረገው እንቅስቃሴ ድርጅቱ ድጋፉን እንደሚጠናክር ማረጋገጡን ጠቁመዋል፡፡