ሚያዝያ 25/2016 (አዲስ ዋልታ) የኢየሱስ ክርስቶስ የስቅለት በዓል በኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን እምነት ተከታዮች ዘንድ በልደታ ማሪያም ካቶሊክ ካቴድራል ቤተክርስቲያን በርካታ የእምነቱ ተከታዮች በተገኙበት በተለያዩ ሃይማኖታዊ ሥነሥርዓት ተከበረ።
የቤተክርስቲያንቱ ሊቀጳጳስ ብፁዕ ካርዲናል ብርሃነ ኢየሱስ ሱራፌል በሥነ ሥርዓቱ ላይ በመገኘት ባስተላለፉት መልዕክት ስቅለት ኢየሱስ ክርስቶስ የሰውን ልጅ ከኃጢአት ለማንፃት ሲል በመስቀል ላይ የተሰቀለበት ሁነት መሆኑን ተናግረዋል።
የዚህም መለኮታዊ መልዕክት ማሳያነቱ ከራስ ባለፈ ለሰው ልጆች ሁሉ ዋጋ መክፈልንና የመልካምነት ሁነኛ ማሳያ መሆኑን አስረድተዋል።
የትንሳኤ በዓልም አጠቃላይ የማካፈልና የመረዳዳት መሆኑን ገልጸው በዓሉን እርስ በእርስ በመተሳሰብ፣ በመደጋገፍ፣ መልካምን ሁሉ በማሰብና በማድረግ ጭምር ልናከብረው ይገባል ብለዋል።
በልደታ ማሪያም ካቶሊክ ካቴድራል ቤተክርስቲያን ስቅለትን ያከበሩት የእምነቱ ተከታዮች በበኩላቸው ስቅለት አንዳችን ለሌላችን ዋጋ መክፈልን የሚያስተምር ነው ሲሉ መናገራቸውን ኢዜአ ዘግቧል።
በመሆኑም የስቅለትን ብሎም የትንሳኤን በዓል ስናከብር ሁላችንም ከራሳችን አልፎ ለሌሎች ማሰብንና ማድረግን ዓላማ አድርገን መሆን አለበት ብለዋል፡፡