ነሀሴ 3/2013 (ዋልታ) – የሶማሌ ክልል በብርቆድ ወረዳ ሻለቃ ከደር መሀሙድ የውትድርና ማሰልጠኛ ማዕከል ሲሰልጥኑ የነበሩ ሚሊሺያ አባላት ዛሬ ተመርቀዋል።
በምርቃ ስነ-ስርዓቱ ላይ የሶማሌ ክልል ምክትል ርእሰ መስተዳድር አቶ ሙስጠፌ ሙሁመድን ጨምሮ ሌሎች የክልሉ ከፍተኛ አመራሮች ተገኝተዋል።
በምርቃቱ ላይ የክልሉ መሠረት ሰላም እና መረጋጋት ነው ያሉት ምክትል ርእሰ መስተዳድሩ አሸባሪው የህወሀት ታጣቂ የሶማሌ ክልልን ለማተራመስ የተለያዩ ሴራዎችን እየሸረበ እንደሆነና ይህ ሴራ እንደሚመከት እርግጠኛ ነኝ ብለዋል።
አቶ ሙስጠፌ አክለውም አሸባሪው ህወሃት ሀገር ለማፍረስ ቢመኝም አቅምና ብቃት እንደሌለው ገልፀው ፡የለመደውን የሀሰት ፕሮፖጋንዳ ሁሉም ዜጋ መታገል አለበት ብለዋል።
የሚሊሻ አባላቱ የሀገራቸውንና የክልላቸውን ሰላም በመጠበቅ በጎሳ ስም ህዝብን ከህዝብ የማጋጨት ስራ የሚሰሩ ሰዎችን መታገል አለባቸው ብለዋል።
በስነ-ስርዓቱ ላይ የሶማሌ ክልል የሰላምና ደህንነት ቢሮ ሀላፊ ዶ/ር ሁሴን ሃሺ ዛሬ የተመረቁት ሚሊሺያዎች የክልሉን ሰላም ለማጠናከር በሚደረገው ጥረት ላይ የጎላ አስተዋጽኦ ይኖራቸዋል ብለዋል።
የሶማሌ ብልፅግና ፓርቲ ፅ/ቤት ሀላፊ ኢ/ር መሀመድ ሻሌ በበኩላቸው ከለውጡ በኋላ እንደ ክልል ትላልቅ ድሎች እንደተመዘገቡ ገልፀው፣ ከድሎቹ መካከልም በክልሉ የሰፈነው አስተማማኝ ሰላም አንዱ እንደሆነ ተናግረዋል።
ሰልጣኞቹ በስልጠና ወቅት የሀገሪቱንና የክልሉን ህገመንግስት፣ የሰብአዊ መብት አያያዝ፣ የመሣሪያ አጠቃቀምና ሌሎች ስልጠናዎችን የወሰዱ ሲሆን በክልሉ ወረዳዎች እንደሚመደቡ መገለፁን የሶማሌ ክልል መገናኛ ብዙሃን ዘግቧል።