የሶማሌ ክልል ካቢኔ ነዳጅን በህገወጥ መንገድ በሚያሸሹ ግለሰቦች ላይ ጠንካራ እርምጃ እንዲወሰድ ወሰነ

መጋቢት 9/2014 (ዋልታ) የሶማሌ ክልል መንግሥት ሥራ አስፈፃሚ አካላት መንግሥት አሁንም ከክልሉ ከተሞች በህገወጥ መንገድ ነዳጅን የሚያወጡና በህገወጥ ተግባር ላይ በተሰማሩ ግለሰቦች ላይ የሚወስደውን ዕርምጃ አጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት ውሳኔ አሳልፏል።

የሶማሌ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ሙስጠፌ ሙሀመድ ከክልሉ ጸጥታ አመራር አካለት፣ አመራሮችና ዞን አስተዳደሪዎች ጋር በክልሉ በተከሰተው ድርቅ ሁኔታ፣ በህገወጥ የነዳጅ ዝውውር፣ በጸጥታና በክልሉ አጠቃላይ ሁኔታ ላይ መክረዋል።

በዚህም ህገ-ወጦች በኅብረተሰቡ ላይ የፈጠሩት ዋጋ ንረትና የነዳጅ እጥረት ችግሮችን ለመቅረፍ እንዲሁም መንግሥት የዜጎችን ኑሮ ለማሻሻል የሚያወጣውን ውሳኔዎች፣ መመሪያዎች እንዲሁም ህግና ደንብ የሚጥሱ አንዳንድ የነዳጅ ማደያ ባለንብረቶች መኖራቸው እንደተረጋገጠና የክልሉ መንግሥት በህገ ወጦቹ ላይ በቂ ትግስት ማሳየቱን ገልፀው አሁን የመንግሥት ትግዕስት ማለቁን ተናግረዋል።

በዚህም ህገ ወጦቹ ከድርጊታቸው ካልተቆጠቡ የንግድ ፍቃዳቸውን እስከመሰረዝ ድረስ ምህረት የሌለ ጠንካራ እርምጃ እንዲወሰድባቸው ከስምምነት ላይ መደረሱን የክልሉ መንግሥት ኮሙዩኒኬሽን መረጃ ያመላክታል፡፡

የህግ የበላይነትን በማጠናከር ህገወጥ እንቅስቃሴዎች መታገልና ሰሞኑን በገዥው ፓርቲ አንደኛ ጠቅላላ ጉባኤ ላይ የተላለፉት ውሳኔዎችና የትኩረት አቅጣጫዎችን ተግባራዊ እንዲደረግ የሶማሌ ክልል መንግሥት ካብኔ አባላት አስምረውበታል።

ለፈጣን መረጃዎች፦
ቴሌግራም https://t.me/WALTATVEth
አብራችሁን ስላላችሁ እናመሰግናለን!