የሸገር ማስዋብ ፕሮጀክቶች በፍጥነትና በጥራት መጠናቀቅ ገበታ ለሀገርን ለመደገፍ አነሳስቶናል- ባለሃብቶች

የሸገርን ማስዋብ ፕሮጀክቶች በፍጥነትና በጥራት መጠናቀቃቸው ገበታ ለሀገርን ለመደገፍ መነሳሳት እንደፈጠረባቸው ባለሃብቶች ገለጹ።

በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ሀሳብ አመንጪነትና በተለያዩ ድርጅቶችና ግለሰቦች ድጋፍ የተከናወኑት የሸገር ማስዋብ ፕሮጀክቶች በአጭር ጊዜ መጠናቀቃቸው ይታወቃል።

ፕሮጀክቶችን ከከተማ ባሻገር አገራዊ ለማድረግ እየተከናወነ ባለው ስራም በርካታ ድርጅቶችና ግለሰቦች በፈቃደኝነት ድጋፍ እያደረጉ ነው።

ከኢዜአ ጋር ቆይታ ያደረጉ ባለሃብቶች የሸገርን ማስዋብ ፕሮጀክቶች በፍጥነትና በጥራት በመጠናቀቃቸው የተሰማቸውን ደስታ ገልጸው፤ ፕሮጀክቶቹ የኢትዮጵያን የተፈጥሮ ሃብት በማልማት በርካታ ቱሪስቶችን ከመሳብ ባለፈ ለዜጎች የሥራ ዕድል በመፍጠር ለምጣኔ ሃብት ዕድገት ጉልህ አስተዋጽኦ እንደሚኖራቸውም ተናግረዋል።

በኢትዮጵያ የልማት ጉዞ አሻራቸውን ማሳረፍ መቻላቸውን እንደ ትልቅ ዕድል የሚቆጥሩት የመሆን ፒ.ኤል.ሲ ሥራ አስኪያጅ ሃርሽ ኮታሪ፤ ድርጅታቸው ለገበታ ለሸገር 5 ሚሊዮን ብር፤ ለገበታ ለአገር ደግሞ የ10 ሚሊዮን ብር ድጋፍ ማድረጉን ገልጸዋል።

“ኢትዮጵያ የውጭ አገር ቱሪስቶችን መሳብ የሚችሉ በርካታ የተፈጥሮ ሃብቶቿን በጥቂቱ በማልማት የመስህብ ስፍራ ማድረግ ተገቢና ትክክለኛ ውሳኔ ነው” ብለዋል።

ገበታ ለሸገር ፕሮጀክት በአጭር ጊዜ እውን ሆኖ ማየታቸው ገበታ ለሀገር ፕሮጀክትን በፈቃደኝነት ለመደገፍ እንዳነሳሳቸውም ጠቅሰዋል።

ለገበታ ለሸገር እና ለገበታ ለሀገር ፕሮጀክቶች አምስት ሚሊዮን ብር ድጋፍ ያበረከቱት የሙለጌ የግል ማኅበር ባለቤትና ሥራ አስኪያጅ አቶ ሙስጠፋ አወል በበኩላቸው በተሰራው ሥራ መደሰታቸውን ገልጸው፤ “ቀደም ሲል ለልማት ተብሎ ከባለሃብቶች የሚሰበሰብ ገንዘብ ለምን ዓላማ እንደዋለ የማወቅ ዕድል አልነበረም” ብለዋል።

አሁን በኢትዮጵያ የተጀመሩ የልማት ፕሮጀክቶች ከታሰቡት በላይ ውጤታማ በመሆናቸው ዜጎች አሻራቸውን እንዲያሳርፉ መልዕክት አስተላልፈዋል።

የፕሮጀክቶቹ እውን መሆን ለቀጣዩ ትውልድ አሻራ ከመጣል ባሻገር የኢትዮጵያን ከፍታ የሚያረጋገጥ እንደሆነም ተናግረዋል።

ከገበታ ለሸገር ፕሮጀክቶች መካከል እንጦጦና አንድነት ፓርኮች እንዲሁም ሸገር የወንዞች ዳርቻ ልማት ሲጠቀሱ፤ ኮይሻ፣ ወንጪና ጎርጎራ ደግሞ በገበታ ለሀገር የሚለሙ ፕሮጀክቶች ናቸው።