ታኅሣሥ 15/2016 (አዲስ ዋልታ) የሸገር ከተማ አስተዳደር 604 ከሚሆኑ ባለሀብቶች ጋር የኢንቨስትመንት ውል ማቋረጡን አስታወቀ።
የሸገር ከተማ ከንቲባ ተሾመ አዱኛ (ዶ/ር) በከተማው ስራቸው የተቋረጡ እና ግንባታቸው የቆመ ኢንቨስትመንቶች የነበሩ መሆኑን ገልጸው በከተማው ለረጅም ዓመታት በባለሀብቶች ተይዘው ወደ ኢንቨስትመንት ያልገቡ መሬቶች መኖራቸውን ጠቁመዋል፡፡
ከ1 ሺሕ በላይ ባለሀብቶች የኢንቨስትመንት መሬትን በህገ ወጥ መንገድ ይዘው መቆየታቸውን የገለፁት ከንቲባው ፈቃድ የተሰጣቸውን ፕሮጀክት መቀየርን ጨምሮ የተለያዩ ችግሮች መኖራቸውን ተናግረዋል።
ችግሩን ለመቅረፍ እርምጃ መወሰዱን ጠቅሰው የነበረውን ውል ማቋረጥ፣ ጽሑፍ ማስጠንቀቂያን ጨምሮ በህግ ወጥ የተያዘ መሬትን ወደ መሬት ባንክ የመመለስ ስራ እየተሰራ መሆኑን አመልክተዋል።
ከተማ አስተዳደሩ ከተቋቋመ ወዲህ ችግሩን ለመቅረፍ እየሰራ መሆኑን ያስረዱት ከንቲባው ኢንቨስትመንት ላይ መሳተፍ የሚፈልጉ አካላት በበይነ መረብ “online” መመዝገብ እንዲችሉ ሁኔታዎች መመቻቸታቸውን ገልጸዋል።
የፊታችን ቅዳሜ ታኅሣሥ 20/2016 ቀን የከተማውን ኢንቨስትመንት የሚያጠናክር የኢንቨስትመንት ፎረም እንደሚካሄድም ተናግረዋል።
በፌናን ንጉሴ