የሸገር ከተማ አስተዳደር 315 ፕሮጀክቶችን አጠናቆ ለአገልግሎት ዝግጁ ማድረጉን አስታወቀ


ሰኔ 24/2016 (አዲስ ዋልታ) የሸገር ከተማ አስተዳደር በ2016 በጀት ዓመት 315 ፕሮጀክቶችን አጠናቆ ለአገልግሎት ዝግጁ ማድረጉን አስታውቋል።

በበጀት ዓመቱ 96 ነባር ፕሮጀክቶችን ጨምሮ የ406 ፕሮጀክቶች ግንባታ በ18 ነጥብ 8 ቢሊዮን ብር እየተከናወነ መሆኑን የከተማ አስተዳደሩ ምክትል ከንቲባ ጉዮ ገልገሎ በሰጡት መግለጫ ተናግረዋል።

ከእነዚህ መካከልም ዲጅታል ሸገርን እውን ለማድረግ የተጀመረውን ፕሮጀክት ጨምሮ 315ቱ ተጠናቀው ለአገልግሎት ዝግጁ መሆናቸውን ነው የገለጹት።

የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥ 2 የኢፋ ቦሩ ትምህርት ቤቶችና 6 አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ግንባታቸው መጠናቀቁንም ጠቁመዋል።

ህሙማን ተኝተው የሚታከሙባቸው 500 አልጋዎች ያሉት ደረጃውን የጠበቀ ሆስፒታልና 5 አዳዲስ ጤና ጣቢያዎች መገንባታቸውንም ጠቅሰዋል።

አዳዲስ ከመገንባት ጎን ለጎን ነባር ተቋማትን ደረጃቸውን የጠበቁ የማድረግ ስራ በጤናው ዘርፍ ከተከናወኑ የልማት ስራዎች ተጠቃሽ ናቸው ብለዋል።

የግብርና ዘርፉን መደገፍ የሚያስችሉ የመስኖ ልማት ፕሮጀክቶች መሰራታቸውን እንዲሁም የመጠጥ ውኃ፣ የከተማ ውበትና ሌሎች ፕሮጀክቶች እንደተጠናቀቁም መግለጻቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

በ2017 በጀት ዓመትም ነባር ፕሮጀክቶችን በፍጥነት በመጨረስ አዳዲስ ፕሮጀክቶችን ለመጀመር መታቀዱን አመላክተዋል።