የሽብር ቡድኑ ዓለማ የትግራይ ህዝብን መከራ በማብዛት የአገዛዝ ስርዓቱን አስከብሮ መቆየት ነው- አቶ ቸርነት ሆርዶፋ

ሐምሌ 01/2013 (ዋልታ) – የሽብር ቡድኑ ህወሓት ዓለማው የትግራይ ህዝብን መከራ በማብዛት የአገዛዝ ስርዓቱን አስከብሮ መቆየት ነው ሲሉ የህግ ባለሙያ የሆኑት አቶ ቸርነት ሆርዶፋ ገለጹ፡፡

የኢትዮጵያ መንግስት ያስተላለፈው የተናጥል የተኩስ አቁም ውሳኔ ለሰብዓዊነት ቅድሚያ የሰጠ እና የዓለምአቀፍ ሕጋዊ ድንጋጌዎችን ያከበረ እንደሆነም ተናግረዋል፡፡

የሽብር ቡድኑ የሰላም አማራጮችን ለመከተል የተለያዩ ቅድመ ሁኔታዎች ማስቀመጡን ያወሱት የሕግ ባለሙያው፣ አሁንም ቢሆን የትግራይ ህዝብን መከራ በማብዛት የአገዛዝ ስርዓቱን አስከብሮ መቆየት አንደሆነ አመልክተዋል፡፡

የኢትዮጵያ መንግስት የተናጥል የተኩስ አቁም ውሳኔ ህወሓትም ሆነ ምዕራባውን ያልጠበቁት ህጋዊ መሰረት እና ተቀባይነት ያለው መሆኑን ያነሱት አቶ ቸርነት፣ መልካም የሚባል ውጤቶችን የሚያስገኝ መሆኑንም አብራርተዋል፡፡

በተባበሩት መንግስታት ቻርተርም ሆነ በሌሎች ዓለም ሀገራት ህግ መሰረት ሁሉም ሀገራት እኩል እና ሉዓላዊ መሆናቸውን የጠቆሙት አቶ ቸርነት፣ ሀገራት በራሳቸው ጉዳይ ላይ የመጨረሻውን ውሳኔ የመወሰን መብትም እንዳላቸው ገልጸዋል፡፡

ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ በኢትዮጵያ ላይ እያሳደረ ያለው ጫና እና የሚታየው ጣልቃ ገብነት ህጋዊ መሰረት የሌለው እና ከእውነታው የራቀ መሆኑን ያነሱት የህግ ባለሙያው፣ ይህ ደግሞ ፈፅሞ ተቀባይነት የሌለው መሆኑን አስምረውበታል፡፡

የኢትዮጵያ መንግስት ሁሉም የፌዴራል እና የክልል ሲቪልና ወታደራዊ ተቋማት ከመንግሥት በሚሰጣቸው ዝርዝር አፈጻጸም መሠረት በትግራይ ክልል የተናጠል ተኩስ አቁም ውሳኔውን እንዲያከብሩ እና እንዲያስከብሩ ማዘዙ ይታወሳል፡፡

የተኩስ አቁሙ “በሰብአዊነት ላይ የተመሰረተ” እንደሆነ የገለጸው መንግስት፣ ተፈጻሚነቱም “ያለ ቅድመ ሁኔታ” የሚከናወን መሆኑን ይፋ በማድረግ ከሰኔ 21 ቀን 2013 ዓ.ም ጀምሮ ተግባራዊ መደረጉ ይታወቃሉ፡፡

(በትዕግስት ዘላለም)