የቀድሞ የመቐለ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ለትግራይ ክልል ድጋፍ አደረጉ

የካቲት 04/2013 (ዋልታ) – በአዲስ አበባ የሚገኙ የቀድሞ የመቐለ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ለሁለት ሳምንታት “እኔም ለወገኔ” በሚል መሪ ቃል ለትግራይ ክልል ሰብዓዊ ድጋፍ የሚውል ከአንድ ሚሊዮን ብር በላይ የሚያወጣ የምግብ ቁሳቁስ አሰባስበው በቀይ መስቀል ማህበር በኩል ድጋፉ ለሚያስፈልጋቸው የህብረተሰብ ክፍሎች እንዲደርስ አስረክበዋል፡፡

የድጋፉ አስተባበሪ አቶ አብዮት በላቸው ሰብዓዊ ድጋፉ ለሚያስፈልጋቸው የትግራይ ክልል ማህበረሰብ ምግብና ምግብ ነክ ቁሶች፣ የንፅህና መጠበቂያ እና ሌሎች ቁሳቁሶችን ያሰባሰብነው ማህበራዊ ሚዲያን ለመልካም ተግባር ለመጠቀም ባደረግነው ጥረት ነው ሲሉ ተናግረዋል፡፡

የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማህበርም በድጋፍ አሰባሳቢ በጎ ፍቃደኞች የተሰበሰበውን የምግብና የንፅህና መጠበቂያ ቁሳቁሶች ወደ ቦታው ወስዶ ለተጎጂዎች እንዲደርስ ተረክቧል፡፡

በበጎ ፈቃደኞች የተሰበሰበው ድጋፍ ኢትዮጵያውያን አንድነታቸውንና አብሮነታቸውን የሚገልጽ እሴታቸውን በእንዲህ አይነቱ ጊዜ እንደሚጠቀሙ ማሳያ ነው ተብሏል፡፡

የኢትዮያ ህዝብ ሁሌም ከትግራይ ህዝብ ጎን መሆኑን የሚያሳይ እንደሆነም ተገልጿል፡፡

ሁሉም ማህበረሰብ በመረባረብ በሃሳብም በቁስም ድጋፍ ከሚያስፈልጋቸው ጋር መሆኑን ማሳየት አለበት ተብሏል፡፡

47 ዓለም አቀፍ ተቋማትና ግብረ ሰናይ ድርጅቶችም በትግራይ ክልል የሰብዓዊ ድጋፍ እንዲሰጡ ተፈቅዶላቸው እንቅስቃሴ እያደረጉ እንደሆነም ታውቋል፡፡

(በምንይሉ ደስይበለው)