የቀድሞ ፕሬዝዳንት ሙላቱ ተሾመ ለኬንያ ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ የኢጋድ የምርጫ ታዛቢ ልዑክን እንዲመሩ ተመደቡ

ሐምሌ 7/2014 (ዋልታ) የኢፌዴሪ የቀድሞ ፕሬዝዳንት ሙላቱ ተሾመ (ዶ/ር) በኬንያ የሚካሄደውን ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ የሚታዘበው የምስራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግሥታት ባለስልጣን (ኢጋድ) የምርጫ ታዛቢ ልዑክን እንዲመሩ ተመድበዋል።

ፕሬዝዳንታዊ ምርጫው ነሐሴ 3 ቀን 2014 ዓ.ም ይካሄዳል።

ኢጋድ የምርጫ ታዛቢ ልዑክ ዶክተር ሙላቱ ተሾመ እንደሚመሩ ዛሬ ባወጣው መግለጫ አስታውቋል።

የኢጋድ ዋና ጸሐፊ ወርቅነህ ገበየሁ (ዶ/ር) “ዶክተር ሙላቱ የምርጫ ልዑክ እንዲመሩ በመመደባቸው ኩራት ይሰማናል፤ በሳል የፖለቲካ መሪና አንጋፋ ዲፕሎማት ናቸው” ብለዋል።

የኬንያ ምርጫ ኮሚሽን ኢጋድ ምርጫውን እንዲታዘብ መፈቅዱ ምስጋናቸውን አቅርበው ተቋሙ የአገሪቷን የዴሞክራሲ ሂደት ድጋፍ እንደሚያደርግ ገልጸዋል።

ዋና ጸሐፊው ፕሬዝዳንታዊ ምርጫው ለኬንያ ሕዝብ ዴሞክራሲያዊ፣ሰላማዊና ስኬታማ እንዲሆን ተመኝተዋል ሲል ኢዜአ ዘግቧል።

ኬንያ የመድብለ ፓርቲ ስርዓትን እ.አ.አ 1991 ካስተዋወቀች በኋላ ለአምስተኛ ጊዜ በሚካሄደው ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ 38 እጩዎች እንደሚሳተፉ የኬንያ የምርጫ ኮሚሽን አስታውቋል።

የቀድሞው የኬንያ ጠቅላይ ሚኒስትር ራይላ ኦዲንጋና የወቅቱ የኬንያ ምክትል ፕሬዝዳንት ዊሊያም ሩቶ ከእጩዎቹ መካከል ይገኙበታል።