የቀጣናው ሀገራት የአሸባሪዎችን የድጋፍ ምንጭ በማድረቅ ስጋት እንዳይሆኑ ትኩረት ሰጥተው ሊሠሩ ይገባል –  ሳሙኤል ተፈራ (ዶ/ር)

ሳሙኤል ተፈራ (ዶ/ር)

ነሐሴ 26/2013 (ዋልታ) – የአፍሪካ ቀንድ ቀጣና አገራት የአሸባሪዎችን የድጋፍ ምንጭ በማድረቅ ስጋት እንዳይሆኑ ትኩረት ሰጥተው በትብብር ሊሠሩ እንደሚገባ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የአፍሪካና እስያ ጥናትና ምርምር ማዕከል ረዳት ፕሮፌሰር ሳሙኤል ተፈራ (ዶ/ር) አመለከቱ፡፡

ዶክተር ሳሙኤል ለአዲስ ዘመን እንደገለጹት፤ ህወሓት፣ ሸኔ፣ አልሸባብና ሌሎች አሸባሪ ቡድኖች በቀጣናው አገራት በሽብር ተግባር ላይ ተሰማርተው ሲሠሩ ቆይተዋል፡፡

ለእነዚህ አሸባሪ ቡድኖች በዓለም አቀፍ ደረጃ በገንዘብ፣ በመሳሪያና በሰው ኃይል ድጋፍ የሚያደርጉ መንግሥታትም ሆኑ ኃይሎች ላይ ትኩረት ሰጥቶ በመሥራት ማንኛውንም ለሽብር ተግባር የሚደረግላቸውን ድጋፍ ማድረቅ እንደሚገባ አመልክተዋል፡፡

በቀጣናው ላይ ትርምስ ለመፍጠር እያደረጉት ያለው ጥምረት እንዳይሳካ ሀገራቱ ከመቼውም ጊዜ በላይ በቅንጅትና በትብብር መሥራት እንዳለባቸው የጠቆሙት ሳሙኤል ተፈራ (ዶ/ር)፣ የአፍሪካ ህብረትና ኢጋድ ቀጣናው የተረጋጋ እንዲሆን በሚደረገው ሂደት የበኩላቸውን አስተዋጽኦ መወጣት እንዳለባቸው ጠቁመዋል፡፡

እንደርሳቸው ማብራሪያ፤ እንደ ሀገር የተረጋጋ ሁኔታ በመፍጠር ለአሸባሪዎች ምቹ ሁኔታ እንዳይኖር መንግሥታት የውስጥ አሠራራቸውን ሊፈትሹ ይገባል፡፡

በእያንዳንዱ እንቅስቃሴ ውስጥ አሸባሪ ቡድኖቹ ምቹ ሁኔታ እንዳያገኙ ህዝቡን የማንቃት ሥራ መሥራትን ያስፈልጋልም ብለዋል፡፡