የቂርቆስ ክፍለ ከተማ ነዋሪዎች ከኢትዮጵያ ነጋዴ ሴቶች ማህበር ጋር በመተባበር ለመከላከያ ስንቅ እያዘጋጁ ነው

ነሃሴ 3/2013(ዋልታ) – የቂርቆስ ክፍለከተማ ወረዳ 02 ነዋሪዎች ከኢትዮጵያ ነጋዴ ሴቶች ማህበር ጋር በመተባበር ለጀግናው የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት ድጋፍ ይሆን ዘንድ ስንቅ እያዘጋጁ ይገኛሉ።

በስንቅ ዝግጅቱ ላይ ያገኘናቸው እናቶች ሀገርን ከወራሪ ለመታደግ ህይወቱን ለሚሰዋው የመከላከያ ሰራዊታችን ያቅማቸውን ከማድረግ ወደኋላ እንደማይሉ ገልፀዋል።

በወረዳው ነዋሪ የሆኑት ወ/ሮ ፀደንያ ከበደ ጠላት ጠላት ሆኖ ከመጣ መልሱ ራስን ከመከላከል ባለፈ ዘምቶ ሀገርን እና ህዝብን ከወራሪ ሀይል መጠበቅ ነው ያሉ ሲሆን ለዚህም ከስንቅ ማዘጋጀት ባለፈ የሚጠበቅብንን ሁሉ ከማድረግ ወደ ኋላ አንልም ብለዋል።

የቂርቆስ ክፍለ ከተማ ወረዳ 02  ስራ አስፈፃሚ አቶ ዳዊት ታደሰ የወረዳው ነዋሪዎች ከዚህ ቀደም 1.8 ሚልየን ብር የሚገመት ድጋፍ በአይነት ለመከላከያ ሰራዊት ማድረጉን አስታውሰው ይህ ሁለተኛው ዙር ድጋፍ 10 ኩንታል ዳቦ ቆሎ እና 10 በግ ለሰራዊቱ ባለበት እንዲደርስ የታቀደ ነው ብለዋል ።

የቂርቆስ ክፍለከተማ ወረደሠ 02 የሴቶች እና ህፃናት ቢሮ ሀላፊ ሰዋረግ አሻግሬ በበኩላቸው ድጋፉ በወረዳው የሚኖሩ ሴቶችን ያማከለ መሆኑን ገልፀው ቀጣይነት ይኖረዋል ብለዋል ።

የሴት ነጋዴዎች ህብረት ከወረዳው ሴቶች እና ህፃናት ጋር በትብብር ያዘጋጀው የስንቅ ድጋፍ የሀገርን ሉአላዊነት ለማስከበር ህይወቱን ያለ ስስት እየሰዋ ላለው ጀግናው  ሰራዊታችን በመሆኑ ዛሬ በጋራ ስንቅ እንዳዘጋጀነው ሁሉ የውጭ ጣልቃገብነትንም በጋራ ማሸነፍ ይጠበቅብናል ያሉት ደግሞ ወ/ሮ እንግዳዬ እሸቴ የኢትዩጵያ ነጋዴ ሴቶች ማህበር ፕሬዝዳንት ናቸው።

(በቁምነገር አህመድ)