የቅባት እህሎችን በስፋት ማምረት ለዘይት ዋጋ መረጋጋት አስተዋጽኦ እንዳለው ተጠቆመ

ሚያዚያ 25/2014 (ዋልታ) የቅባት እህሎችን በስፋት ማምረት የዘይት ምርት ዋጋን ለማረጋጋት አስተዋጽኦ እንዳለው በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የኢንዱስትሪ እና ማዕድን ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አስታወቀ፡፡

ቋሚ ኮሚቴው በኮከብ ቃና የዘይት ፋብሪካ የመስክ ምልከታ ያደረገ ሲሆን፤ ፋብሪካው የዘይት ምርት ለሕብረተሰቡ በስፋት የማቅረብ ዓቅም ያለው ቢሆንም፤ ባጋጠመው የግብዓት ዕጥረት ምክንያት በዓቅሙ ልክ ማምረት እንዳልቻለ ከተደረገለት ገለጻ ተረድቷል፡፡

ፋብሪካው የገበያውን ሁኔታ ለማረጋጋት እና የዘርፉን ምርታማነት ለማሳደግ፤ ከሌሎች ኢንዱስትሪዎች ጋር በቅንጅት መሥራቱን፣ ቋሚ ኮሚቴው በጥንካሬ ተመልክቶታል፡፡

ይሁን እንጂ የዘርፉን ምርታማነት አሁን ካለበት በተሻለ ለማሳደግ ግብዓት ሊያቀርቡ ከሚችሉ ድርጅቶች እና አርሶ-አደሮች ጋር በበለጠ ቅንጅት መሥራት እንደሚያስፈልግ ጠቁሞ፤ ጥሬ ዕቃዎችን በሀገር ውስጥ ለማምረት በትኩረት ሊሠራ እንደሚገባ አሳስቧል፡፡

ድርጅቱ በአጠቃላይ በግብይት ሥርዓቱም ሆነ በምርት ጥራት ደረጃው ላይ ቁጥጥር በማድረግ፤ የጀመረውን የገበያ ማረጋጋት ሥራ አጠናክሮ እንዲቀጥል ቋሚ ኮሚቴው በግብረ-መልሱ አሳስቧል፡፡

የፋብሪካው የአስተዳደር ዳይሬክተር ሚካኤል ካሳ በበኩላቸው በቀን 165 ቶን ዘይት የሚያጣራው ይህ ፋብሪካ በዓመት አንዴ የሚያገኘው የቅባት እህል፣ ከሦስት ወር በላይ የሚያሠራው ባለመሆኑ፤ መሥራት ካለበት ከሃያ በመቶ በታች እየሠራ ይገኛል ብለዋል።

ድፍድፍ ዘይት ከውጭ በማስገባት እና በስፋት በማምረት፤ በተመጣጣኝ ዋጋ ለመንግስት ሠራተኞች፣ ለሸማች ማኅበራት እንዲሁም ለተለያዩ የንግድ ተቋማት ምርቱን በማድረስ፤ የተከሰተውን የዘይት ዕጥረት ችግር ለመቅረፍ የተሻለ መሠራቱን ዳይሬክተሩ አያይዘው አብራርተዋል፡፡

ዳይሬክተሩ አክለውም፤ የቅባት እህሎች በሚመረቱባቸው ቦታዎች ያለውን የጸጥታ ችግር በመፍታት፣ መንግስት የበኩሉን ሚና እንዲወጣ እና የባንኮች ድጋፍ እንደያስፈልጋቸው መጠቆማቸው የምክር ቤቱ መረጃ አመላክቷል፡፡