ሰኔ17/2013 (ዋልታ) – የሶማሌላንድ ፕሬዝዳንት ሙሳ ቢሂ፣ የኢፌዴሪ ከፍተኛ ልኡካን እና የዲፒ ወርልድ ዳይሬክተር ሱልጣን ቢን ሱለይማን በተገኙበት የበርበራ ወደብ የመጀመሪያ ዙር ማስፋፊያ ፕሮጀክት ተመርቆ በይፋ ሥራውን ጀምሯል።
በዲፒ ወርልድ 51 በመቶ፣ በሶማሊላንድ 30 በመቶ እና በኢትዮጵያ 19 በመቶ ድርሻ የተያዘው የበርበራ ተርሚናል ኮርደር የመጀመሪያ ዙር ማስፋፊያ ፕሮጀክት 500 ሺህ ኮንቴነሮችን መያዝ የሚችል ተርሚናል እንደሆነና በአመት አንድ ሚልዮን ኮንቴነሮችን ማስተናገድ ይችላል ተብሏል።
ወደቡ ዘመናዊ ክሬኖች እንደተገጠሙለትና ከዛሬ ጀምሮ ግዙፍ መርከቦችን በማስተናገድ ለቀጠናው በተለይ ለኢትዮጵያ ትልቅ ጥቅም እንዳለው ተገልጿል።
የኢፌዴሪ ትራንስፖርት ሚኒስትሯ ወ/ሮ ዳግማዊት ሞገስ በስነ-ሥርአቱ እንዳሉት ኢትዮጵያ የ10 አመት የኢኮኖሚ ፕላን እንደቀየሰችና የኢትዮጵያ ወጪና ገቢ ለማሳደግ ወደቦችን ማልማትና መጠቀም አስፈላጊ በመሆኑ የበርበራ ወደብ መከፈት ለኢኮኖሚው ትልቅ ሚና አለው።
የኢፌዴሪ ገንዘብ ሚኒስትር አቶ አህመድ ሽዴ በበኩላቸው፣ የበርበራ ወደብ የመጀመሪያው ዙር ተርሚናል ስራ መጀመር በቀጣናው የኢኮኖሚ ውህደትን ከፍ እንደሚያደርግና በተለይ በየጊዜው እያደገ የሚገኘው የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ለማሳለጥ በበርበራ ወደብ ላይ ለሚደረገው ስራ ኢትዮጵያ ትካፈላለች ብለዋል።
አቶ አህመድ ሽዴ አክለውም ከበርበራ ወደብ ኢትዮጵያ በተለይ የሶማሌ ክልል ተጠቃሚ እንደሚሆን ገልፀው፣ ኢትዮጵያ ከበርበራ-ጅግጅጋ-ድሬዳዋ-ኤረር-ሚኤሶ መንገድ በመገንባት ጅግጅጋንና ድሬዳዋን ከበርበራ ወደ ምስራቅ ኢትዮጵያ የኮንቴነር መዳራሻ እንደሚሆን ተናግረዋል።
የሶማሌ ክልል ምክትል ርእሰ መስተዳድር አቶ ሙስጠፌ ሙሁመድ በበኩላቸው፣ የሶማሌላንድ ልማትና እድገት የኢትዮጵያ በተለይ የሶማሌ ክልል እድገት እንደሆነ ጠቁመው፣ የበርበራ ወደብ ለቀጣናው ህዝብ ፋይዳው የጎላ ነው ብለዋል።
የሶማሌላንድ ፕሬዝዳንት ሙሳ ቢሂ ለኢትዮጵያ በተለይ ለሶማሌ ክልል ደረጃውን የጠበቀ የወደብ አገልገሎት እንደሚሰጡና ከወደብ የሚወርዱ እቃዎች በሰላም ወደ መዳረሻቸው እንዲደርሱ ይደረጋል ብለዋል።
የበርበራ ወደብ ዛሬ ወደ አዲስ አበባ የሚጓዙ ኮንቴነሮችን ከመርከብ በማራገፍ ሥራውን በይፋ መጀመሩን የሶማሌ ማስ ሚዲያ ዘገባ ያመለክታል።