የ’በቃ’ ዘመቻ አካል የሆነ ሰልፍ በአውስትራሊያ ሜልቦርን ተካሄደ

ታኅሣሥ 3/2014 (ዋልታ) የ’በቃ’ ወይም ‘#NoMore‘ ዘመቻ አካል የሆነ ሰላማዊ ሰልፍ በአውስትራሊያ ሜልቦርን ከተማ በአውስትራሊያ ፓርላማ ፊት ለፊት ተካሄደ።

ሰልፈኞቹ ባሰሙት መፈክር የምዕራቡ ዓለም አንዳንድ አገራት በኢትዮጵያ ላይ እያደረጉት ያለውን ያልተገባ ጫናና ጣልቃ ገብነት አውግዘዋል።

የምዕራባውያኑ መገናኛ ብዙኃን በኢትዮጵያ ላይ የሚያሰራጯቸውን ሀሰተኛ ዘገባዎችን እንዲያቆሙና ዓለም ዐቀፉ ማኅበረሰብ አሸባሪው ሕወሓት በአማራና አፋር ክልሎች የፈጸማቸውን በደሎች እንዲያወግዙ ጠይቀዋል።

አሸባሪው የሕወሓት ቡድን ድርጊቶች በዓለም ዐቀፍ ወንጀል የሚያስጠይቅ እንደሆነም አስገንዝበዋል።

‘ኢትዮጵያ አትፈርስም፣ ኢትዮጵያ ታሸንፋለች፣ ከኢትዮጵያ ሕዝብና መንግስት ጎን ነን፣ ዓለም ዐቀፉ ማኅበረሰብ በሕዝብ ድምጽ የተመረጠውን መንግስት ማክበርና እውቅና መስጠት አለበት’ የሚሉና ሌሎች ‘የበቃ’ እንቅስቃሴ መልዕክቶች በሰልፉ ላይ ተላልፈዋል።

በሰላማዊ ሰልፉ ላይ በአውስትራሊያ የኢትዮጵያ ኮሙዩዩኒቲ አባላትና የኢትዮጵያ ወዳጆች መሳተፋቸውን ኤዜአ ከሰልፉ አዘጋጆች ያገኘው መረጃ ያመለክታል።

ሰልፉን ያዘጋጁት በአውስትራሊያ የኢትዮጵያ ኮሙዩዩኒቲ አባላት መሆናቸው ተገልጿል።

‘የበቃ’ ወይም ‘#NoMore‘ ዘመቻ አካል የሆኑ ሰላማዊ ሰልፎች ዛሬ በዴንማርክ ኮፐንሀገንና በግሪክ አቴንስ ይካሄዳሉ። የ’#NoMore‘ ዘመቻ እንቅስቃሴ አፍሪካ፣ አውሮፓ፣ እስያ፣ ሰሜን አሜሪካና ኦሺኒያ አህጉራትን አዳርሷል።