የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳድር ምክትል ከንቲባ ወ/ሮ አዳነች አቤቤ የበጎ ፍቃድ አገልግሎት ተግባራት የአብሮነታችን ማሳያ ነው ሲሉ ገለጹ።
ምክትል ከንቲባ ወ/ሮ አዳነች የገና በዓልን ምክኒያት በማድረግ በጉለሌ ክፍለ ከተማ አስተባባሪነት በክፍለ ከተማው እና በሱሉልታ ከተማ በበጎ ፍቃደኞች ለአቅመ ደካማ ነዋሪዎች የታደሱ ቤቶችን አስረክበዋል።
ልማት ሁሉንም ማህበረሰብ አካታች መሆን አለበት ያሉት ወ/ሮ አዳነች መሰል የወሰን ተሻጋሪ እና ሌሎች የበጎ ፍቃድ አገልግሎቶች የህዝብ ለህዝብ ግንኙነትን የሚያጠናክሩ በመሆኑ ተጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባ ተናግረዋል።
በዓሉን በማስመልከት የአቅመ ደካማ የነዋሪዎች ቤት የማደስ እና የተለያዩ ድጋፍ እንዲደረግ አስተዋጽኦ ላበረከቱ በጎ ፍቃደኞች፣ የከተማዋ ነዋሪዎች እና አመራሮች ምክትል ከንቲባዋ አመስግነዋል፡፡
የጉለሌ ክፍለ ከተማ ዋና ስራ አስፈጸሚ አቶ አባወይ ዮሐንስ የገና በዓልን በማስመልከት በክፍለ ከተማው በርካታ ተግባራት መከናወኑን ገልጸው በወሰን ተሻጋሪ የበጎ ፍቃድ አገልግሎት የሱሉልታ ከተማን ጨምሮ 73 የአቅመ ደካማ ቤት እድሳት መደረጉን ገልጸዋል፡፡
ለአቅመ ደካማ ነዋሪዎች፣ ለፌደራል እና ለአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን አባላት 39 የእርድ ሰንጋ በሬዎች፣ 114 በጎች እና ግምታቸው 3.8 ሚሊየን ብር የተለያዩ አልሚ ምግቦችና አልባሳት ድጋፍ መደረጉን ከከንቲባ ጽህፈት ቤት ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡