የቡና አምራች አርሶ አደሮችን በቀጥታ ተጠቃሚ የሚያደርግ አዲስ የግብይት ሥርዓት ሊጀመር ነው

ግንቦት 16/2013 (ዋልታ) – የቡና አምራች አርሶ አደሮችን በቀጥታ ተጠቃሚ የሚያደርግ አዲስ የግብይት ሥርዓት “ማይክሮሎት ትሬዲንግ ፕላትፎርም” ሊጀመር ነው።
የቡና እና ሻይ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር አዱኛ ደበላ አዲሱ የማይክሮሎት የቡና ግብይት ሥርዓት ከስከዛሬው የተለየና በኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ የሚተገበር መሆኑን ገልጸዋል፡፡
በተለይም መጠናቸው ዝቅተኛ ቢሆንም በከፍተኛ ጥራት ተዘጋጅተው እና በላቦራቶሪ ምርመራ ከ85 በመቶ በላይ የጥራት ደረጃ ውጤት የተሰጣቸው እንዲሁም የምርት ዱካቸው የሚታወቅ ቡናዎችን ለማገበያየት ምቹ እንደሆነም ጠቁመዋል።
የግብይት ሥርዓቱ አርሶ አደሮችን ተጠቃሚ የሚያደርግ እንዲሁም ከፍተኛ ጥራት ያለውን ቡና ለሀገር ውስጥ ቡና ላኪዎች በከፍተኛ ዋጋ በኢትዮጵያ ምርት ገበያ እንዲገበያይ ያስችላልም ተብሏል፡፡
በቡና ስራው ላይ ለፍተው እና ደክመው ቡናን ለአለም ገበያ በማቅረብ ከፍተኛ አስተዋፅኦ የሚያበረክቱ አርሶ አደሮችን ተጠቃሚ እንደሚያደርግም ተገልጿል።
የኢትዮጵያ ምርት ገበያ ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ ወንድምአገኘሁ ነገራ በበኩላቸው፣ የኢትዮጵያ ምርት ገበያ ላለፉት 13 ዓመታት ከሁሉም የሀገሪቱ ባንኮች ጋር በግብይት በመተሳሰር በመረጃ የተደገፈ የግብይት ሥርዓት ዘርግቶ ሲሰራ መቆየቱን አስታውሰዋል፡፡
የባለ ልዩ ጣዕም ቡና ልዩ ግብይት በከፍተኛ ዋጋ የሚከናወን በመሆኑ ምርት ገበያው ለግብይቱ ስኬታማነት ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት ጋር በጥምረት ይሰራል ብለዋል።
አዲሱ የግብይት ፕላትፎርም ግንቦት 23/2013 ዓ.ም የሚጀምር ሲሆን፣ ለባለ ልዩ ጣዕም ዓለም አቀፍ ውድድር ቀርበው በብሄራዊ ደረጃ አሸናፊ የሆኑትን አርሶ አደሮች ቡና በማገበያየት ይጀመራል ተብሏል።
(በቁምነገር አህመድ)