የባለሥልጣኑ የምርምር የልህቀት ማዕከል ግንባታ በመጠናቀቅ ላይ መሆኑ ተገለጸ


ሰኔ 29/2013 (ዋልታ) – በምስራቅ አፍሪካ ቀዳሚ እንደሚሆን የሚጠበቀው የኢትዮጵያ መንገዶች ባለስልጣን የምርምር የልህቀት ማዕከል ግንባታ በመጠናቀቅ ላይ መሆኑ ተገለጸ።

ዓለም አቀፍ የምርምር ደረጃዎችን አሟልቶ እየተገነባ የሚገኘው የምርምር የልህቀት ማዕከሉ ዋና ዋና የግንባታ ስራዎቹ እየተጠናቀቁ ሲሆን፣ ቀሪ ክንውኖችን ለመፈጸም በትኩረት እየተሰራ ነው ተብሏል።

በበማዕከሉ የመስክ ምልከታ የተደረገ ሲሆን፣ የላቦራቶሪ የግንባታ ስፍራዎች፣ የቢሮ እና የመሰበሰቢያ አዳራሽ፣ የተመራማሪዎች አፓርትመንት፣ የእንግዳ ማረፊያንና የሰራተኞች ሬስቶራንት ግንባታ መፀናቀቁ ተገልጿል።

ማዕከሉ በዘመናዊ መልኩ ይበልጥ መደራጀቱ የመንገድ ሀብትን ሳይንሳዊ በሆነ መልኩ ለመምራት፣ ለማስተዳደርና ለመገንባት የላቀ አበርክቶት እንዳለው ተመልክቷል፡፡

በቀጣይ ውስን በሆኑ አፍሪካ ሀገራት ብቻ የሚገኙ የምርምር መሳሪያዎችን የሚያሟላ ይሆናልም ነው የተባለው።

ዘመናዊ የፍተሻ መሳሪያዎች የሚኖሩት በመሆኑ በብዙ አፍሪካ ሀገራትም ተመራጭ የምርምር ማዕከልም ያደረገዋል ተብሏል።

ማዕከሉ ሙሉ ለሙሉ ሲጠናቀቅ ከምርምርና ከቴክኖሎጂ ሽግግር ስራው ባሻገር የውጭ ምንዛሬ በማምጣት ረገድም የራሱ የሆነ አስተዋጽኦ እንደሚኖርው ከባለስልጣኑ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።