የባልደረቦቹን የይለፍ ቃል በመጠቀም ከ7 ነጥብ 3 ሚሊዮን በላይ ብር ባጭበረበረው የባንክ ሠራተኛ ላይ ክስ ተመሠረተ

ጥቅምት 18/2015 (ዋልታ) የሥራ ባልደረቦቹን የይለፍ ቃል በመጠቀም ከ7 ነጥብ 3 ሚሊዮን ብር በላይ ከሁለት የባንኩ ደንበኞች አካውንት ወደ ሌላ ግለሰብ ያስተላለፈው የአቢሲኒያ ባንክ ሠራተኛ ላይ ዐቃቤ ሕግ ክስ መሥርቷል።

የዐቃቤ ሕግ የክስ መዝገብ እንደሚያመላክተው አዲሱ ብርሀኑ የተባለው አንደኛ ተከሳሽ በአቢሲኒያ ባንክ የአስኮ ንዑስ ቅርንጫፍ የደንበኞች አገልግሎት መኮንን ሆኖ ሲሠራ ለራሱ ጥቅም ለማግኘት ወይም ለሌላ ሰው ለማስገኘት በማሰብ የሁለት ጓደኞቹን የይለፍ ቃል በመጠቀም በቀን 06/01/2015 ዓ.ም ከቀኑ 7:50 ሰዓት ሲሆን የቅርንጫፍ ባንኩ ሠራተኞች ለምሳ በወጡበት ሰዓት የተሰጠውን ኃላፊነት ያለአግባብ በመገልገል፣ የባንኩ የአያት ባቡር ቅርንጫፍ ደንበኛ ከሆኑት ተቋመች ወ/ጊዎርጊስ ሒሳብ ቁጥር ላይ 3 ሚሊየን 251 ሺሕ  ብር ቀንሶ ወደ ሌላ የባንኩ ደንበኛ ለሆነው ወደ አበበ ሙላቱ ሒሳብ ቁጥር አስተላልፏል።

በቀን 07/01/2015 ዓ.ም ከጥዋቱ 1:41 ሰዓት ሲሆን ጠዋት ማንም ሠራተኛ ሥራ ሳይገባ ቀድሞ በመግባት የባንኩ የለገሀር ቅርንጫፍ ደንበኛ ከሆኑት ፍሬወይኒ ዓባይ ሒሳብ ቁጥር ላይ 4 ሚሊየን 100 ሺሕ ብር ቀንሶ ወደ ሌላ የባንኩ ደንበኛ ሳሚ ጌታቸው ሒሳብ ቁጥር ያስተላለፈ ሲሆን፣ በድምሩ 7 ሚሊየን  351 ሺሕ  ብር ከሒሳብ ባለቤቶቹ ፈቃድ እና እውቅና ውጪ የሁለት የሥራ ባልደረቦቹን የይለፍ ቃል በመጠቀም በማስተላለፍ እና ግብይቱን በማጽደቅ ጉዳት ያደረሰ በመሆኑ የሙስና ወንጀሎችን ለመደንገግ በወጣው አዋጅ ቁጥር 881/2007 አንቀጽ 9(2) በመተላለፍ በፈፀመው ሥልጣንን አላግባብ መገልገል የሙስና ወንጀል ተከሷል።

በተያያዘም ዐቃቤ ሕግ በክስ መዝገቡ ላይ ሁለተኛ ተከሳሽ ገመቹ ታከለ የባንኩ ቢዝነስ ኦፊሰር እንዲሁም ሦስተኛ ተከሳሽ ምንአለሸዋ መንግሥቱ የባንኩ ኦፕሬሽን ኦፊሰር የሆኑት ተከሳሾች ራሳቸው ብቻ ሊይዙት እና ሊጠብቁት የሚገባውን ኮድ ማወቅ ለማይገባው ሰው በቸልተኝነት እንዲያውቀው በማድረጋቸው በፈፀሙት የሕዝባዊ ድርጅት ሥራን በማያመች አኳኋን መምራት ወንጀል ተከሰዋል።

ዐቃቤ ሕግም የሰው እና የሰነድ ማስረጃዎችን በማጠናቀር በመሠረተው ክስ ላይ የፌዴራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ ችሎት ለኅዳር 16 ቀን 2015 ዓ.ም ተከሳሾች የክስ መቃወሚያቸውን እንዲያቀርቡ ትዕዛዝ መስጠቱን የፍትሕ ሚኒስቴር መረጃ ያመለክታል።