የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ በህክምና ዘርፍ ያሰለጠናቸውን ተማሪዎች እያስመረቀ ነው

የካቲት 19/2014 (ዋልታ) የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ የሕክምና እና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ በተለያዩ የትምህርት ዘርፎች ያሰለጠናቸውን 457 ተማሪዎች እያስመረቀ ነው፡፡

ኮሌጁ 383 በቅድመ ምረቃ፣ 24 በማስተርስ እንዲሁም በሕክምና ስፔሻሊቲ 50 በድምሩ 457 ተማሪዎችን ነው እያስመረቀ የሚገኘው፡፡ ከተመራቂዎቹ መካከልም 187 ሴቶች መሆናቸው ታውቋል፡፡

ኮሌጁ ከተቋቋመበት ጀምሮ በቅድመ ምረቃ 2 ሺሕ 456፣ በድኅረ ምረቃ 805፣ በሕክምና ስፔሻሊቲ 219፣ በሶስተኛ ዲግሪ 6 በድምሩ 3 ሺሕ 486 ተማሪዎችን አስመርቋል።

የሕክምና እና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ የአገሪቱን የጤና ሥርዓት ለማሻሻል፣ ለማኅበረሰቡ ጥራት እና ተደራሽነት ያለው የሕክምና አግልግሎት መስጠት የሚችሉ ባለሙያዎችን በማፍራት የበኩሉን አስተዋፅኦ እያበረከተ መሆኑን ገልጿል፡፡

በአሁኑ ሰዓትም ኮሌጁ 2 ሺሕ 363 ተማሪዎችን እያስተማረ እንደሚገኝ ከዩኒቨርሲቲው ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡