ጥቅምት 18/2017 (አዲስ ዋልታ) ለይፋዊ የስራ ጉብኝት ቻይና የሚገኘው የብልጽግና ፓርቲ ከፍተኛ የልዑካን ቡድን የቻይና ኮሚኒስት ፓርቲ የዓለም አቀፍ ግንኙነት ዲፓርትመንት ጋር ተወያይቷል።
የልዑካን ቡድኑን የሚመሩት የብልጽግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዚዳንት አደም ፋራህ ከዲፓርትመንቱ ምክትል ሚኒስትር ሊ ሚንሽያንግ ጋር የሁለትዮሽ ውይይት አድርገዋል።
በውይይቱ ወቅት የፓርቲ ለፓርቲ፣ የመንግስት ለመንግስት እና የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነትን ይበልጥ ማጠናከር የሚያስችሉ በርካታ ሃሳቦች ተነስተዋል።
የፓርቲው ምክትል ፕሬዚዳንት አደም ፋራህ ቻይና እና ኢትዮጵያ ረጅም ታሪክ ያላቸው ሀገራት መሆናቸውን በማውሳት በሁሉም ዘርፎች ጠንካራ ግንኙነት እንደተመሰረተ ማብራራታቸውም ከብልጽግና ፓርቲ የተገኘው መረጃ ያመላክታል።
በተጨማሪም የፓርቲ ለፓርቲ ግንኙነቱ በልምድ ልውውጥ፣ በትምህርትና ስልጠና እንዲሁም በሌሎች የአቅም ግንባታ ድጋፎች ተጠናክሮ መቀጠሉን እና ወደፊትም ይበልጥ አብረው ለመስራት ብልጽግና ፓርቲ ዝግጁ መሆኑን ገልጸዋል።
የቻይና ኮሚኒስት ፓርቲ የዓለም አቀፍ ግንኙነት ዲፓርትመንት ምክትል ሚኒስትር ሊ ሚንሽያንግ በበኩላቸው ኢትዮጵያ እና ቻይና ግንኙነታቸውን ጽኑ ወዳጅነት በሚባል ደረጃ ማድረሳቸውን ተናግረዋል።
ይህንን አስጠብቆ ለመቀጠል ያላቸውን ዝግጁነት በመግለጽም ሁለቱ ፓርቲዎች የገነቡት የረጅም ጊዜ ትብብርም የመንግስት ለመንግስት ግንኙነቱን በሚያጠናክር ደረጃ መድረሱን አንስተዋል።