የብልፅግና ፓርቲ የሴቶች ሊግ የ6 ወራት የስራ አፈፃፀሙን እየገመገመ ነው

የብልፅግና ፓርቲ የሴቶች ሊግ የስድስት ወራት የስራ አፈፃፀም ግምገማ እያደረገ ነው፡፡

ሴቶች በልማት፣ ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እንዲሁም ፖለቲካዊ ዘርፍ ንቁ ተሳታፊ እንዲሆኑ አለፍ ሲልም ስኬታማ አፈፃፀም እንዲኖራቸው መርህ ያደረገው ሊጉ ባለፉት ስድስት ወራት የሴቶችን ሁለንተናዊ ብልፅግና ለማረጋገጥ ሲሰራ መቆየቱ ተገልጿል::

በሊጉ በየዘርፉ የሴቶችን ተሳትፎ ከመጨመር አኳያ የተሰሩ ስራዎች ጥንካሬያቸው እንዲቀጥል እና ተግዳሮቶች እልባት እንዲያገኙ የስራ አፈፃፀም ግምገማ ማድረግ መቻሉ ፋይዳው የላቀ መሆኑ ተጠቁሟል::

የሴቶች አደረጃጀትን በመጠቀም ለሀገራዊ ተልዕኮዎች የመንግስት አቅጣጫን በመከተል በግንባር ቀደምትነት በንቅናቄዎች ቅድሚያ ትግል በማድረግ፣ የአካባቢያቸውን ሰላም በማስጠበቅ፣ በሀገሪቱን የህግ የማስከበር ዘመቻ ተሳትፎ በማድረግ፣ የእናቶችና ህፃናት ሞትን በመቀነስ፣ የቁጠባ ባህልን በማዳበር እና የቦንድ ግዥ በመፈጸም ላይ ከፍተኛ ስራ መሰራቱም ተገልጿል፡፡

በተጨማሪም የአረንጓዴ አሻራ ቀዳሚ ተሳታፊ በመሆን ብሎም ከሀገር አልፎ ለአለም ስጋትና ቀውስ ምክንያት የሆነው የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ለመግታት በሚደረገው ርብርብ የሴቶች አደረጃጀት ሚናው ከፍተኛ ነው ተብሏል፡፡

(በሄብሮን ዋልታው)