የብሔራዊ ስታዲየም ግንባታ እንዲፋጠን እየተሰራ መሆኑ ተገለጸ

ሰኔ 10/2014 (ዋልታ) የብሔራዊ ስታዲየም ግንባታ እንዲፋጠን እየተሰራ መሆኑን የባህልና ስፖርት ሚኒስትሩ ቀጄላ መርዳሳ ተናገሩ።

ሚኒስትሩ በዛሬው ዕለት የብሔራዊ ስታዲየም ግንባታ ሂደትን ተዘዋውረው ጎብኝተዋል።

ከስፖርታዊ ክንውኖች ባሻገር የአዲስ አበባ ተጨማሪ ውበትና ድምቀት ይሆናል ተብሎ የሚታሰበው የብሔራዊ ስታድዬም ሁለተኛ ምዕራፍ የማጠቃለያ እና የፊኒሽግ ሥራ እየተሰራ ይገኛል።

በአዲስ አበባ ቦሌ አካባቢ በቻይናው ስቴት ኮንስትራክሽን ኢንጂነሪንግ ኩባንያ እየተገነባ ያለው እና ከስፖርታዊ ክንውኖች ባሻገር የአዲስ አበባ ተጨማሪ ውበትና ድምቀት ይሆናል ተብሎ የሚታሰበው የብሔራዊ ስታዲየም 62 ሺህ ስዎችን የመያዝ አቅም ያለው ሲሆን የመጀመሪያው የግንባታ ምዕራፍ ተጠናቆ በአሁኑ ወቅት የሁለተኛው ምዕራፍ እና የማጠቃለያ ሥራው በመገንባት ላይ ይገኛል።

በዛሬው ዕለትም የባህልና ስፖርት ሚኒስትሩ ቀጄላ መርዳሳ የስታዲየሙን የግንባታ ሂደት እና የደረሰበትን ደረጃ ተዘዋውረው ጎብኝተዋል።
ሚኒስትሩ በጉብኝታቸው ወቅት እንደገለፁት እየተገነባ የሚገኘው ስታዲየም ግዙፍ መሆኑን እና በርካታ የፊኒሽግ ስራዎች መሰራታቸውን ጠቅሰው ፤ በተለይ ከሁለት ወራት ወደዚህ በስታዲየሙ ውስጣዊ እና ውጫዊ የማጠቃለያ ስራዎች ተሰርተዋል ብለዋል ።
ነገር ግን ግንባታው በሚፈለገው ፍጥነት እየሄደ ባለመሆኑ የግንባታ ተቋራጩ ስራውን እንዲያፋጥን ግፊት እየተደረገ መሆኑን ገልፀዋል።
በተለይም የውጭ ምንዛሬ ሳያስፈልጋቸው በሀገር ውስጥ ጥሬ ዕቃዎች ሊሰሩ የሚችሉ ስራዎች እንዲፋጠኑ እና ከውጭ የሚገቡ የግንባታ እቃዎች በወቅቱ በማስገባት ግንባታው በሚፈለገው ጊዜ እንዲጠናቀቅ ከግንባታ ተቋራጩ ጋር ውይይት እየተደረገ መሆኑንም ሚኒስትሩ አክለዋል ።
ከአለም የግንባታ እቃዎች መናር ጋር ተያይዞ የዋጋ ጭማሪ እንዲደረግላቸው በግንባታ ተቋራጩ በኩል ጥያቄ እየቀረበ መሆኑን ያነሱት ሚኒስትሩ፤ የሀገሪቱን የግንባታ ህግ ተከትሎ አሁን ባለው የገብያ ዋጋ ማስተከከያ ይደረጋልም ብለዋል ።
እንደ መንግስት ግንባታው እንዳይቋረጥ እና በፍጥነት እንዲጠናቀቅ አስፈላጊውን ድጋፍ ለማድረግ ዝግጁ ነን ፤ በተቋራጩ በኩልም ግንባታውን ለማጠናቀቅ ቁርጠኝነታቸውን ገልፀውልናል ሲሉ መናገራቸውን ከሚኒስቴሩ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።
በሁለተኛው ምዕራፍ የማጠቃለያ ሥራ ሙሉ የስታዲየሙ የውስጥ የቀለም ሥራ፣ የኤሌክትሮ መካኒካል ፣ የውሃና የኤሌክትሪክ ፣ የተመልካች መቀመጫ ኢፓክሲ ፣ የጣራ ተሸካሚ ምሰሶዎች ፣ የተጠናቀቁ ሲሆን የተመልካች መፀዳጃ ቤቶች ኮርኔስ እና የሴራሚክ ንጣፍ ስራ እና የውጪ ሜዳዎች እየተሰራ ይገኛል።