የቦሌ ክፍለ ከተማ ለሀገር መከላከያ ሰራዊት ከ13 ሚሊዮን ብር በላይ የአይነት ድጋፍ አደረገ

ኅዳር 20/2014 (ዋልታ) የቦሌ ክፍለ ከተማ ለጀግናው የሀገር መከላከያ ሰራዊት ግንባር ድረስ በመምጣት ከ13 ሚሊዮን ብር በላይ የአይነት ድጋፍ አደረገ።

ድጋፉን ያስረከቡት የክፍለ ከተማው ስራ አስፈፃሚ አለምፀሀይ ሽፈራው እንደ ክፍለ ከተማ  ከዚህ በፊት 107 ሚሊየን ብር ድጋፍ አድርገናል፤ አሁንም ደግሞ ደጀንነታችን ለማሳየት  ማህበረሰብ ያዋጣውን 13 ሚሊየን ብር የሚያወጣ የአይነት ድጋፍ ይዘን በመምጣት ለሰራዊታችን አስረክበናል ብለዋል።

የከተማው ማህበረሰብ ለሰራዊቱ ደጀን ለመሆን ሁሌም ዝግጁ መሆኑን ገልጸው በቀጣይም አጠናክረን እንቀጥላለን ሲል ገልጸዋል።

በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የአዲስ አበባ የፋይናስ ቢሮ ኃለፊ ነጅባ ከማል ለሀገር መከታ ለሆነው የሀገር መከላከያ ሰራዊት ድጋፍ እንደከተማ አስተዳደር ለ3ኛ ጊዜ የተሰባሰበ አስታውሰው ክፍለ ከተሞችም ከማህረሰቡ ጋር በመሆን ድጋፋቸውን አጠናክረው መቀጠላቸውን ገልፀዋል።

በጦር ግምባር ተገኝተን የኢትዮጵያን አሸናፊነት ከሚያረጋግጠው ሰራዊታችን ጎን በመገኘታችንና  በመደገፋችን ደስ ይለናል፤ ሁሌም አብረናችሁ እንደሆንን እገልፃለሁ ሲሉም አበረታተዋል።

በግንባር ድጋፋን የተቀበሉት ሌተናል ኮሎኔል ለቺሳ መገርሳ ከማህበረሰቡ እየመጣ ያለው ድጋፍ ደጀንነቱን እያስመሰከረ ለሰራዊቱም ሞራል እየሆነው ነው ብለዋል።

ሰንጋና የተለያየ የአይነት ድጋፍ ተቀብለናል፤ ለዚህም በሰራዊቱ ስም ምስጋና አቀርባለሁ ሲሉም አክለዋል።

በምንይሉ ደስይበለው (ከግንባር)