ሐምሌ 23/2013 (ዋልታ) – የቦንጋ ዩኒቨርሲቲ ለሁለተኛ ጊዜ በተለያዩ የትምህርት ዘርፎች ያሰለጠናቸውን 821 ተማሪዎች አስመርቋል።
የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝዳንት ዶ/ር ጴጥሮስ ወ/ጊዮርጊስ ተመራቂዎች አስቸጋሪውን የኮቪድ 19 ወረርሽኝ በመከላከልና ተፅእኖውን በመቋቋም ለዛሬው ቀን በመብቃታችሁ እንኳን ደስ ያላችሁ ብለዋል።
የዘንድሮው የምረቃ በአል ዩኒቨርሲቲው ባስመዘገበው የላቀ አፈፃፀም ሁለት አገር አቀፍ ሽልማቶችን በተጎናፀፈ ማግስት የተደረገ እንደመሆኑ አይረሴ ያደርገዋል ሲሉ ፕሬዝዳንቱ ገልፀዋል።
በሌላም በኩል ሀገራችን የታላቁን ህዳሴ ግድብ ሁለተኛ ዙር የውሃ ሙሌት ባከናወነች ማግስት እንዲሁም መላው ኢትዮጵያዊያን አሸባሪውን የህወሃት ቡድን ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ለመደምሰሰ በአንድነት በቆሙበት ወቅት የተደረገ በመሆኑ በብዙ መልኩ የተለየ ነው ብለዋል።
በ2013 በጀት አመት በካፋ ዞን ከሚገኙ 12 ወረዳዎች ጋር በተፈጠረ መልካም ግንኙነትና በዞኑ አስተዳደር ድጋፍ እያንዳንዱ ወረዳ ለዩኒቨርሲቲው የምርምር ስራ የሚሆን 500 ሔክታር መሬት ካርታ አዘጋጅቶ ለዩኒቨርሲቲው ማስረከቡንም ዶ/ር ጴጥሮስ ተናግረዋል።
ዩኒቨርሲቲው በመማር ማስተማር፣ ጥናትና ምርምር እንዲሁም በህብረተሰብ አገልግሎት ዘርፎች ላይ በርካታ ተግባራት ማከናወኑን አስረድተዋል።
ዋልታ ሚዲያና ኮሚዩኒኬሽን ኮርፖሬት የዩኒቨርሲቲውን በጎ ተግባራት ለህዝብ ይፋ በማድረግ ዩኒቨርሲቲው ላስመዘገበው የላቀ አፈፃፀም አጋዥ በመሆኑ ምስጋና ይገባዋልም ብለዋል።
የትምህርት ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ እና የበአሉ የክብር እንግዳ ዶ/ር ሙሉ ነጋ በበኩላቸው የቦንጋ ዩኒቨርሲቲ በአረንጓዴ አሻራ፣ በበጎ ፈቃድ አገልግሎት፣ በጥናት እና ምርምር ስራዎችና መሰል ተግባራት የላቀ አፈፃፀም ማስመዝገቡን ጠቁመዋል።
የዛሬ ተመራቂዎችም ወደ ስራ በሚሰማሩበት ጊዜም የተጣለባቸውን ሀገራዊ እና ሙያዊ ሃላፊነታቸውን በታማኝነት እንዲወጡ አሳስበዋል።
በምረቃ ስነ ስርአቱ ላይ የትምህርት ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ ዶ/ር ሙሉ ነጋ፣ የፌደራል ሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽን ኮሚሽነር በዛብህ ገብረየስና የቦንጋ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ዶ/ር ጴጥሮስ ወ/ጊዮርጊስን ጨምሮ የዩኒቨርሲቲው የቦርድ አባላትና አመራሮች የችግኝ ተከላ አከናውነዋል።
(በነስረዲን ኑሩ)