የተለያዩ ተቋማትና ግለሰቦች ለሀገር መከላከያ ሰራዊት ድጋፍ አደረጉ

ኅዳር 21/2014 (ዋልታ) የተለያዩ ተቋማትና ግለሰቦች ለሀገር መከላከያ ሰራዊት ድጋፍ አድርገዋል፡፡

በዚህም የኢፌዴሪ ፕሬዝዳንት ጽህፈት ቤት፣ በደቡብ ሱዳን የኢትዮጵያ ኮሙዩኒቲ፣ ባለሀብቶች እንዲሁም የኮርያ ዘማች የሆኑ ጥንዶች ድጋፍ አድርገዋል።

ድጋፍ አድራጊዎቹ በየግንባሩ የሀገሩን ኅልውና ለማስጠበቅ ህይወቱን እየተሰጠ ለሚገኘው ሰራዊት የገንዘብ ድጋፍ ማድረግ ከሰራዊቱ ትግል አንጻር ተመጣጣኝ ባይሆንም ከሰራዊቱ ጎን መሆናችንን ያሳይልናል ብለዋል።

ሁሉም በሚችለው ሁሉ ከአገር መከላከያ ሰራዊት ጎን መሆን አለበት ያሉት ድጋፍ አድራጊዎቹ ለሀገር ኅልውና አደጋ የሆነው አሸባሪው ሕወሓት ከኢትዮጵያ ምድር እስኪወገድ ድረስ ድጋፋችንን እንቀጥላለን ሲሉም ገልጸዋል።

ድጋፉን የተከረቡት የመከላከያ ሚኒስትር ዴኤታ ማርታ ልዊጂ በበኩላቸው ለሰራዊቱ የሚደረገው ድጋፍ ተጠናክሮ መቀጠሉን አንስተው አሸባሪው ትሕነግ በአውደ ውግያ ከከፈተው ግንባር በተጨማሪ በተለያዩ መስኮች ግንባር ፈጥሯል ብለዋል፡፡ ኅብረተሰቡም ይህንን በመረዳት በልማት፣ በዲፕሎማሲ፣ በኢኮኖሚ እና ሌሎች ዘርፎች የበኩሉን እያደረገ ከሰራዊቱ ጎን መሰለፍ እንዳለበት ገልጸዋል።

በመስከረም ቸርነት