የተለያዩ ወንጀሎችን ሲፈጽሙ የነበሩ የሽብር ቡድን አባላት በቁጥጥር ሥር ዋሉ

መስከረም 20/2015 (ዋልታ) ከባድ የግድያ፣ የውንብድና እና የዘረፋ ወንጀልን ሲፈጽሙ የነበሩ የሽብር ቡድን አባላት በቁጥጥር መዋላቸውን የፀጥታና ደኅንነት የጋራ ግብረ-ኃይል አስታወቀ።

የሽብር ተልዕኮ ተቀብለው በንፁሃን ዜጎች ላይ ሦስት የግድያ፣ አንድ የመግደል ሙከራ፣ 46 በጦር መሣሪያና በድምጽ አልባ የስለት መሣሪያዎች የታገዘ የዘረፋና የውንብድና ወንጀሎችን በመፈፀም ሕብረተሰቡ በሥጋት እንዲኖር ሲያደርጉ የነበሩ ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ሥር መዋላቸውን ነው የጋራ ግብረ-ኃይሉ ያስታወቀው፡፡

ከህወሓት የሽብር ቡድን ጋር በመቀናጀት በአዲስ አበባ ከተማ፣ ሞጆ፣ ዝዋይ፣ ሻሸመኔ፣ ቱሉቦሎ፣ በወሊሶ፣ ቡታጅራና በወልቂጤ በሚወስዱ መንገዶች ላይ በአራት ቡድን ተደራጅተው የፌዴራልና የክልል የፀጥታ አካላትን የደንብ ልብስና አንፀባራቂ ልብስ በመልበስ፣ ከፍተኛ የብርሃን ኃይል ያለው ባውዛ እና በጦር መሣሪያ በመታገዝ ተሽከርካሪዎችን እያስቆሙ ከባድ የዘረፋና የግድያ ወንጀል ሲፈጽሙ የነበሩ የኦነግ ሸኔ አባላት፡-

1. አብደላ ከድር ፣
2. ቦና አያኖ ፣
3. ታሪኩ ሲርባ ፣
4. ቃሲም ገመቹ ፣
5. ዲታ ካሼ ፣
6. መሐመድ አደም፣
7. ጫላ ወንድሙና
8. ጀማል ከድር
የተባሉት ተጠርጣሪዎች የራይድ ተሽከርካሪዎችን በከፍተኛ ገንዘብ በመኮናተር ወደ ክልል ከተሞች በመውሰድ የተለያዩ ሰበቦችን በመፍጠር ካመሹ በኋላ በሌሊት ወደ አዲስ አበባ እንሂድ በማለት በጉዞ ላይ ሳሉ ጨለማና ጭር ያለ ቦታ ሲደርሱ አሽከርካሪውን በማስቆም የአሽከርካሪዎችን አንገት በስለት ወግቶ በመግደል በአሽከርካሪዎች ላይ አሰቃቂ ወንጀል መፈፀማቸውን ሁሉም ተጠርጣሪዎች አምነው የወንጀል ቦታውንና አፈፃፀማቸውን ለምርመራ ቡድኑ መርተው አሳይተዋል፡፡

በሽብር ተግባራት ላይ የተሰማሩት የህወሓትና የሸኔ የሽብር ቡድኖች በሀገር ላይ ግልጽ ጦርነት ከፍተው ንፁሃንን በጅምላ በመግደል ሕዝቡን ስሜት ውስጥ በማስገባት ሀገሪቱ ወደ ለየለት ብጥብጥ እንድትገባ ለማድረግ የሸረቡት ሴራ ሳይሳካላቸው ሲቀር በአዲስ አበባና በሌሎች ከተሞች የግድያና የዘረፋ ቡድኖች በማሰማራት የከተማ ውስጥ ሽብርና ጦርነት ለመፈጠር ሲቀንቀሳቀሱ እንደነበር ግብረ-ኃይሉ እንደደረሰባቸውም አመልክቷል።

የሽብር ድርጊቱ ተሳታፊዎች በፀጥታና ደኅንነት የጋራ ግብረ-ኃይሉ ብርቱ ክትትልና በህብረተሰቡ መረጃ ሰጪነት ሁሉም የወንጀሉ ተሳታፊዎች በቁጥጥር ስር ማዋሉን ገልጾ አዲስ አበባ እና ሌሎች የሀገራችን ከተሞች ከመሰል የሽብር እና የወንጀል ድርጊቶች የመከላከልና ወንጀሎቹም ተፈጽመው ሲገኙ ተጠርጣሪዎችን በህግ ቁጥጥር ሥር የማዋል ተግባር ተጠናክሮ እንደሚቀጥል የፀጥታና ደኅንነት የጋራ ግብረ-ኃይል አሳስቧል፡፡

በተመሳሳይ ሁኔታ በሀረርና በድሬዳዋ በተለያዩ አካባቢዎች የአድራሻ ለውጥ እያደረገች የሸኔን የሽብር ቡድን በህቡዕ ስታደራጅ የነበረችው የሽብር ቡድኑ ከፍተኛ አመራር ጫልቱ መሐመድ አብዲ በቅጽል ስሟ (ጃል ቦንቱ ጉሚ) ተብላ የምትጠራው ተጠርጣሪ በኦነግ ሸኔ የሽብር ቡድን በኬኒያ ሶሎሎ የውትድርና እና የካድሬ ስልጠና ወስዳ ወደ ሽብር ቡድኑን ተቀላቅላ ጃል ገመቹ አቦዬ ከሚባል የሸኔ ሽብር ቡድን ከፍተኛ አመራር ጋር እየተገናኘች ወጣቶችን በመመልመል ወደ ኬኒያ ሶሎሎ ማሰልጠኛ እየላከች የሽብር ቡድኑን እንዲቀላቀሉ በማድረግና ኢትዮ-ኬኒያ ድንበር ድረስ በመዘዋወር ከ2010 ዓ.ም ጀምሮ የሽብር ተግባር ስትፈጽም ቆይታ በቅርቡ በተደረገው ኦፕሬሽን በድሬዳዋ ከተማ ከ13 ግብረ አበሮቿ እና ኤግዚቢቶች እንዲሁም ከተለያዩ ሚስጥራዊ ሰነዶች ጋር በቁጥጥር ሥር መዋሏን ግብረ-ኃይሉ ለዋልታ በላከው መረጃ አመላክቷል።

ለፈጣን መረጃዎች፦
ፌስቡክ https://bit.ly/3Ma7QTW
ቴሌግራም https://t.me/WALTATVEth
ዩቲዩብ https://www.youtube.com/c/WaltaTV/featured
ቲዊተር https://twitter.com/walta_info
አብራችሁን ስለሆናችሁ እናመሰግናለን!