የተለያዩ የአፍሪካ አገራት ውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች አዲስ አበባ ገቡ

ጥር 24/2014 (ዋልታ) የኒጀር፣ ጂቡቲ፣ ደቡብ አፍሪካ፣ ሴኔጋል፣ ሊቢያና ሞሪታኒያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች አዲስ አበባ ገቡ።

በ35ኛው የአፍሪካ ኅብረት የመሪዎች ጉባኤ እና በ40ኛው የአስፈፃሚ ምክር ቤት ስብሰባ ላይ ለመሳተፍ የኒጀር ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሀሱሚ ማሹዱ፣ ጂቡቲው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሙሀሙድ አሊ የሱፍ፣ የሊቢያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ናጅላ አልማንጉሽ እና የሞሪታኒያ አረባዊ ሪፐብሊክ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር እስማኤል ኡልድ ሼክ አሕመድ ለሊት ላይ አዲስ አበባ ገብተዋል።

ማለዳ ላይም የደቡብ አፍሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ናለዲ ፓንዶር (ዶ/ር) እና የሴኔጋል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አሲታ ቶል ሳል አዲሰ አበባ መግባታቸውን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ጽ/ቤት ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

ሚኒስትሮቹ ቦሌ ዓለም ዐቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ሲደርሱ የኢፌዴሪ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የካቢኔ ጉዳዮች ዋና ሹም አምባሳደር ምህረተዓብ ሙሉጌታ እና የፕሮቶኮል ጉዳዮች ሹም አምባሳደር ፈይሰል አሊይ አቀባበል አድርጎላቸዋል፡፡