የተለያዩ የውጭ አገራት ገንዘቦችን ሲመነዝሩ የነበሩ 7 ግለሰቦች በቁጥጥር ስር ዋሉ

በመጋቢት 9/2014 (ዋልታ) በቦሌ ክፍለ ከተማ በሞባይል ስልክ መሸጫ እና በሸቀጣ ሸቀጥ መደብር ውስጥ በህገ-ወጥ መልኩ የተለያዩ የውጭ አገራት ገንዘቦችን ሲመነዝሩ የነበሩ ሰባት ግለሰቦች በቁጥጥር ስር መዋላቸውን የአዲስ አበባ ፖሊስ ገለጸ፡፡

መጋቢት 8 ቀን 2014 ዓ.ም በቦሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ 3 ልዩ ቦታው ሸገር ህንፃ ማክ ሞባይል ስልክ መሸጫ እና ወረዳ 4 ልዩ ቦታው አውራሪስ ሆቴል አካባቢ በሚገኝ የሸቀጣሸቀጥ መሸጫ ሱቆች ላይ ፖሊስ ባደረገው ፍተሻ በርካታ ገንዘቦች ተይዘዋል፡፡

የክፍለ ከተማው ፖሊስ መምሪያ በጥናት ላይ ተመስርቶ በህግ አግባብ ባከናወነው ብርበራ ከሁለቱም ሱቆች በአጠቃላይ ከ762 ሺሕ በላይ የኢትዮጵያ ብር፣ 19 ሺሕ 65 የአሜሪካ ዶላር፣ 17 ሺሕ 750 ዩሮ፣ 40 የእንግሊዝ ፓውንድ፣ 3 ሺሕ 800 የካናዳ ዶላር ተገኝቷል፡፡

በተጨማሪም የሩሲያ፣ የተባበሩት አረብ ኢሚሬት፣ የፈረንሳይ፣ የአውስትራሊያ፣ የኤርትራ፣ የሱዳን፣ የስዊድን፣ የቻይና፣ የባህሬን እና የኳታር መገበያያ ገንዘቦች በኤግዚቢትነት መያዙን ከቦሌ ክፍለ ከተማ ፖሊስ መምሪያ የተገኘው መረጃ ያሳያል፡፡

በወንጀሉ የተጠረጠሩ 7 ግለሰቦችም በቁጥጥር ስር ውለው ምርመራ እየተጣራባቸው እንደሚገኝም ተገልጿል፡፡

ህገ-ወጥ የገንዘብ ምንዛሬ አገርን እየጎዳና የኑሮ ውድነትን ከእለት ወደ እለት እያባባሰ ያለ ተግባር መሆኑን ኅብረተሰቡ ተገንዝቦ የውጭ አገር ገንዘቦችን በባንክ ብቻ መመንዘር እንደሚገባ እና ማንኛውም ሰው ተመሳሳይ ተግባር የሚፈፅሙ ህገ-ወጦችን በሚመለከትበት ወቅት ለፀጥታ አካላት ጥቆማ መስጠቱን አጠናክሮ እንዲቀጥል የአዲስ አበባ ፖሊስ ጥሪውን አቅርቧል፡፡

ለፈጣን መረጃዎች፦
ቴሌግራም https://t.me/WALTATVEth
አብራችሁን ስላላችሁ እናመሰግናለን!