የተረጂነት አስተሳሰብና ተግባርን በማስቀረት ክልሉን የብልጽግና ተምሳሌት ማድረግ አንደሚገባ ተገለጸ


ግንቦት 22/2016 (አዲስ ዋልታ) የተረጂነት አስተሳሰብና ተግባርን በማስቀረት ክልሉን የብልጽግና ተምሳሌት ማድረግ ይገባናል ሲሉ የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል የመንግሥት ዋና ተጠሪ ፀጋዬ ማሞ ተናገሩ፡፡

የክልሉ አደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽን “ከተረጂነት ወደ ምርታማነት፤ ለተሟላ ሀገራዊ ሉዓላዊነትና ክብር” በሚል መርህ ሀሳብ የንቅናቄ መድረክ በቴፒ ከተማ አካሂዷል።

በመድረኩ ላይ የተገኙት የክልሉ የመንግሥት ዋና ተጠሪ ፀጋዬ ማሞ ክልላዊ ምርት እና ምርታማነትን በማሻሻል ትርጉም ባለው መልኩ ተረጂነትን ማስቀረት ይገባናል ብለዋል።

መንግሥት ባለፉት ቅርብ ዓመታት የውጭ ተረጂነትን ለማስቀረት በበጋ የመስኖ ስንዴ ተግባር አመርቂ ውጤት ማስመዝገቡን ገልጸው ይህንን ተሞክሮ በሌሎች መስክም ተግባራዊ በማድረግ የተረጂነት አስተሳሰብና ተግባርን በማስቀረት ክልሉን የብልጽግና ተምሳሌት ማድረግ እንደሚገባ ተናግረዋል።

በክልሉ ልመናን የሚፀየፍ ማህበረሰብ በመፍጠር የእርዳታ ጠባቂነት ማስቀረት እንደሚገባ ጠቅሰው ጠንካራ ኢኮኖሚ በመገንባት የብልጽግና ጉዞውን ለማስቀጠል በሚደረገው ጥረት በየደረጃው ያለው አመራር ተገቢውን ትኩረት እንዲሰጥ አሳስበዋል።

የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድርና የግብርና ቢሮ ኃላፊ ማስረሻ በላቸው በበኩላቸው የሀገር ክብርና ብልጽግናን ለማረጋገጥ ልመናና ተረጂነትን ማስቀረት አንገብጋቢ ጉዳይ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በክልሉ ያሉ የልማት ፀጋዎችን አሟጦ በመጠቀም የምግብ ዋስትናን ማረጋገጥ እንደሚገባም በአጽንዖት አስገንዝበዋል።

በክልሉ በተፈጥሮ አደጋ የሚከሰቱ ችግሮችንና ሌሎች ሰብዓዊ ድጋፎችን በራስ አቅም ለማቋቋም የሚያስችል አቅም ለመፍጠር ምርትና ምርታማነትን ማሳደግ፣ የሥራ ባህል ማሳደግ እና የተረጂነት አስከፊነት በህብረተሰቡ ዘንድ ማስረጽ ይገባልም ብለዋል።

ከተረጅነት አስተሳሰብ ለመላቀቅና በቤተሰብ ደረጃ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ ምርታማነትን መጨመር ተቀዳሚ ተግባር መሆኑን የገለጹት ደግሞ የክልሉ አደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽን ኮሚሽነር ለማ መሰለ (ዶ/ር) ናቸው።

ኮሚሽነሩ ስትራቴጂካዊ ዕቅዱ በክልሉ በተለያዩ ማዕቀፎች የሚደጎሙ ተረጂዎችን በቀጣዮቹ 2 ዓመታት ውስጥ ሙሉ በሙሉ ለማላቀቅ ግብ ያደረገ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በመድረኩ የክልሉ አስተባባሪ ኮሚቴ አባላት እና ሌሎች የክልልና የዞን ከፍተኛ የመንግሥት የስራ ኃላፊዎች መገኘታቸውን የክልሉ ኮሙዩኒኬሽን መረጃ አመላክቷል፡፡