የተስፋ ብርሃን ምገባ ማዕከልን ለመገንባት የሚያስችል ስምምነት ተፈረመ

ሰኔ 3/2014 (ዋልታ) ዘመን ባንክ አክሲዮን ማኅበር እና አዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የተስፋ ብርሃን ምገባ ማዕከልን በጋራ ለመገንባት የሚያስችል የስምምነት ውል ዛሬ ተፈራርመዋል።

ለአቅመ ደካማ ዜጎች መመገቢያ ማዕከል ሆኖ እንደሚያገለግል የተገለጸው የምገባ ማዕከሉ ግንባታ ወጪ ሙሉ በሙሉ በዘመን ባንክ የሚሸፈን ሲሆን ከ8 ሚሊዮን ብር በላይ እንደሚጠይቅም ተነግሯል።

በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የአዲስ አበባ ከተማ ዋና ሥራ አስኪያጅ ጥራቱ በየነ በፊርማ ሥነ ሥርዓቱ ላይ ባደረጉት ንግግር ከተማ አስተዳደሩ ሰው ተኮር ፕሮጀክቶችን በመንደፍ የከተማውን ሕዝብ በተለየ ሁኔታ ተጠቃሚ ለማድረግ ሰፊ ርብርብ እየተደረገ መሆኑን ገልፀዋል።

ሥራውን ለማሳካት የባለሃብቶችና ተቋማት እገዛ ከፍተኛ እንደነበረ ገልጸው የዘመን ባንክ አ.ማ አመራርና ቦርድ ለዚህ በጎ ጥሪ በጎ ምላሽ በመስጠታቸውንም ምስጋና አቅርበዋል፡፡

የዘመን ባንክ አ.ማ ሥራ አስፈፃሚ ደረጀ ዘበነ ከተማ አስተዳደሩ ለሚሰራቸው ሥራዎች ባንኩ ከጎኑ እንደሚቆም መግለጻቸውን ከአዲስ አበባ ከተማ ኮሙዩኒኬሽን ቢሮ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

ለፈጣን መረጃዎች፦
ፌስቡክ https://bit.ly/3Ma7QTW