የተሻለ አፈፃፀም ላስመዘገቡ ሆስፒታሎች የእውቅና ስነ ስርአት እየተካሄደ ነው

ሐምሌ 28/2013 (ዋልታ) – የ2013 ዓ.ም ሀገር አቀፍ የኢትዮዽያ ሆስፒታሎች በጥምረት ለጥራት ፕሮግራም የተሻለ አፈፃፀም ላስመዘገቡ የመንግስት ሆስፒታሎች የእውቅና ስነ ስርአት እየተካሄደ ይገኛል::

የሆስፒሎችን አገልግሎት አሰጣጥ የማዘመን እሳቤን አንግቦ በጤና ሚኒስቴር ሀሳብ ጠንሳሽነት የዛሬ 9 አመት የተጀመረው የጥምረት ለጥራት የመለኪያ መስፈርት በዛሬው እለት 3ተኛ ዙር ውድድሩን በመንግስት ሆስፒታሎች መካከል በማድረግ የተሻለ አፈፃፀም ላስመዘገቡ ሆስፒታሎች የእውቅና የሽልማት እና ምስጋና መርሀ ግብሩን አካሂዷል::

የጤና ሚኒስትሯ ዶ/ር ሊያ ታደሰ በበኩላቸው ይህ የመለኪያ መስፈርት በሆስፒታሎች መካከል የእርስ በእርስ የመማሪያ መድረክ ከመሆን አንስቶ ያለባቸውን ውስንነት ከመሙላት አኳያ እንዲሁም የሚሰጡትን አገልግሎት በማሻሻል አለም የደረሰበት የአሰራር ዘይቤን የዋጀ አገልግሎት እንዲሰጥ ከማድረግ አኳያ ጠቀሜታው የጎላ መሆኑን አንስተዋል::

በዚህ አመትም የጤና ተቋማት ለህሙማን ምቹ እና ፅዱ እንዲሁም መረጃን መሰረት ያደረጉ ተቋማትን ለመፍጠር መስፈርትን ይዞ ሲንቀሳቀስ ቆይቷል በየዙሩም የተያዩ የትኩረት አቅጣጫዎችን በመምረጥ የጤና ተቋማትን ለማብቃት ተሰርቷል ተብሏል::

በቀጣይ በሆስፒታሎች መካከል ያለውን ጥምረት በማጠናከር የጤና ዘርፉን የሚፈለግበት ደረጃ ላይ ለማድረስ የነበሩ አና አዲስ የሚረቁ አጀንዳዎችን መሬት ላይ በማውረዱ ረገድ ሁሉም ባለ ድርሻ አካል የበኩሉን አስተዋፅዖ እንድዲያበረክት ዶ/ር ሊያ ታደሰ ጥሪያቸውን አቅርበዋል::
(በሄብሮን ዋልታው)