የተቋሙን ደህንነት በማረጋገጥ ረገድ የአየር ኃይል ጥበቃ ክፍለ ጦር ውጤታማ ተግባር እያከናወነ መሆኑ ተገለጸ

ሐምሌ 26/2015 (ዋልታ) የተቋሙን ደህንነት በማረጋገጥ ረገድ የአየር ኃይል ጥበቃ ክፍለ ጦር ውጤታማ ተግባር እያከናወነ መሆኑን የኢፌዴሪ አየር ኃይል ዋና አዛዥ ሌተናል ጄኔራል ይልማ መርዳሳ ገለጹ፡፡

ሌተናል ጄኔራል ይልማ መርዳሳ በጥበቃ ክፍለ ጦር የሥራ ቦታ የተሰሩት ቢሮዎች፣ የመዝናኛ ቦታዎች እና የልማት ስራዎችን ተዘዋውረው ጎብኝተዋል።

የአየር ኃይል ጥበቃ ክፍለ ጦር የተቋሙን ደህንነት እና ዋስትና ከማረጋገጥ ባለፈ ከዚህ በፊት እንደችግር ሲነሱ የነበሩ ክፍተቶችን በአጭር ጊዜ በአስተማማኝ ሁኔታ በማስወገድ የአየር ኃይልን የግዳጅ አፈፃፀም ውጤታማ ማድረግ መቻሉንም ገልጸዋል።

የጥበቃ ክፍለ ጦሩ አባላት በቢሾፍቱ እና አካባቢው ጭምር የኅብረተሰቡን ሰላም በመጠበቅ ፅንፈኞችን በመታገል አኩሪ ተግባር መፈጸማቸውን አዛዡ ተናግረዋል።

የክፍሉ አባላት ከግዳጅ ጎን ለጎን በራስ ተነሳሽነት የሥራ ቦታቸውን እና አካባቢያቸውን ለማልማት ያደረጉት ጥረት ለሌሎችም የተቋሙ ክፍሎች ምሳሌ መሆኑን ሌተናል ጀኔራል ይልማ መርዳሳ ገልጸዋል።

የአየር ኃይል ጥበቃ ክፍለ ጦር አዛዥ ኮሎኔል ወንዱ ወልዱ በበኩላቸው የጥበቃ ክፍለ ጦሩ ለሚሰጠው ማንኛውም ተልዕኮ የተለየ ትኩረት በመስጠት ግዳጁን በሚገባ እየተወጣ እንደሚገኝ ገልፀዋል።

ኮሎኔል ወንዱ የአየር ኃይል አዛዥ እና ከፍተኛ አመራሮች ያደረጉት ልዩ ክትትል እና ድጋፍ የጎላ አስተዋፅኦ እንደነበረው ጠቁመው የአየር ኃይል አዛዥ የሰጡት አስተያዬት የሥራ ተነሳሽነትን እና ሞራልን የሚገነባ ነው ማለታቸውን ከኢፌዴሪ መከላከያ ሠራዊት ማኅበራዊ ትስስር ገጽ ያገኘነው መረጃ አመላክቷል።