የተባበሩት መንግሥታት፣ ፈረንሳይና አምነስቲ ኢንተርናሽናል የመንግሥት የሰላም ውሳኔ መልካም እርምጃ መሆኑን ገለጹ

መጋቢት 17/2014 (ዋልታ) የተባበሩት መንግሥታት፣ ፈረንሳይ እና አምነስቲ ኢንተርናሽናል መንግሥት ለሰብኣዊነት ሲባል ግጭት ለማቆም መወሰኑ መልካም እርምጃ መሆኑን ገለጹ።

የመንግሥታቱ ድርጅት ዋና ጸሐፊ አንቶኒዮ ጉተሬዝ በቃል አቀባያቸው ስቴፋኒ ዱጃሪች በኩል ባወጡት መግለጫ የኢትዮጵያ መንግሥት ለሰብኣዊነት ሲባል ግጭት ለማቆም መወሰኑን እንደሚያደንቁ ተናግረዋል፡፡

የመንግሥት ውሳኔ በፍጥነት ተግባራዊ እንዲሆንም ሁሉም አካላት የበኩላቸውን አስተዋጽኦ ማድረግ እንደሚጠበቅባቸው አስገንዝበዋል፡፡

ለጋሾች እና ግብረ-ሰናይ ድርጅቶች በትግራይ፣ በአማራ እና በአፋር ክልሎች በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ለሚገኙ ዜጎች የሚያደርጉትን ድጋፍ በእጥፍ እንዲያሳድጉም ጥሪ አቅርበዋል።

የፈረንሳይ መንግሥት በበኩሉ በመግለጫው እንዳስታወቀው የመንግሥትን እርምጃ እንደሚያደንቅ እና ውሳኔው በትግራይ ክልል ለሚገኙና ለችግር ለተጋለጡ ሰዎች ድጋፍ ለማቅረብ የሚደረገውን ጥረት እንደሚያቀላጥፍ ገልጿል፡፡

የመንግሥት ውሳኔ ለችግር ለተጋለጡ ሰዎች አስፈላጊውን ድጋፍ ለማቅረብ ምቹ ሁኔታ እንደሚፈጥር ጠቅሶ ሁሉም አካላት ሊቀበሉት እንደሚገባና አፈጻጸሙንም በቅርብ እንደሚከታተል አስታውቋል፡፡

ፈረንሳይ የልማት አጋሮቿን በማስተባበር ድጋፍ እንደምታሰባስብ እና በኢትዮጵያ በሁሉም አካባቢዎች ለጉዳት የተጋለጡ ዜጎችን ለመደገፍ ቁርጠኛ እንደሆነች ተገልጿል፡፡

በተመሳሳይም አምነስቲ ኢንተርናሽናል ባወጣው መግለጫ የመንግሥትን ውሳኔ አዎንታዊ ሲል ገልጾ የሰብኣዊ እርዳታ አቅርቦቱ በትግራይ ብቻ ሳይሆን በአማራ እና አፋር ክልሎችም ጭምር ለጉዳት ለተጋለጡ ሁሉ እንደሚገባ አስገንዝቧል፡፡

እንደኢዜአ ዘገባ የአምነስቲ ኢንተርናሽናል የምስራቅ አፍሪካ እና የአፍሪካ ቀንድ አካባቢ ቢሮ ምክትል ዳይሬክተር ሳራ ጃክሰን የመንግሥትን ውሳኔ ሁሉም አካላት ሊያከብሩት እና የበኩላቸውን አስተዋጽኦ ሊያበረክቱ ይገባል ብለዋል፡፡