የተባበሩት መንግስታት ለኢትዮጵያ 40 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር መደበ

ኅዳር 6/2014 (ዋልታ) የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ለኢትዮጵያ ከአደጋ ጊዜ ፈንድ 40 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር ዛሬ መመደቡን አስታወቀ።
የመንግስታቱ የሰብዓዊ ድጋፍ ኃላፊ ማርቲን ግሪፊትዝ እንዳስታወቁት ገንዘቡ በግጭቱ ሰለባ ለሆኑ ዜጎች የህይወት አድን እገዛ የሚውል ነው።
ገንዘቡ በሰሜኑ የአገሪቱ ክፍል የተፈጠረው ግጭት ያስከተለውን ቀውስ እና በደቡብ ኢትዮጵያ ለተከሰተው ድርቅ ምላሽ ለመስጠት ከፍ ያለ አቅም የሚፈጥር እንደሆነም ተገልጿል።
ከዚህ ውስጥ 25 ሚሊዮን ዶላሩ ለህይወት አድን ሰብዓዊ ድጋፍና ሲቪሎችን ለመጠበቅ ከማዕከላዊ የአደጋ ጊዜ ምላሽ ፈንድ (ሲ.ኢ.አር.ኤፍ) የተመደበ ሲሆን ቀሪው 15 ሚሊዮን ዶላር ደግሞ በኢትዮጵያ የሰብዓዊ ፈንድ (ኢ.ኤች.ኤፍ) የተመደበ መሆኑን የኢዜአ ዘገባ ያመለክታል።