የተባበሩት አረብ ኢምሬቶች ፕሬዝዳንት የኢትዮጵያ ጉብኝት በሀገራቱ ታሪካዊ ግንኙነት አዲስ ምዕራፍ የከፈተ ነው – አምባሳደር መለሰ ዓለም

አምባሳደር መለሰ ዓለም

ነሔሴ 18/2015 (አዲስ ዋልታ) የተባበሩት አረብ ኢምሬቶች ፕሬዝዳንት የኢትዮጵያ ጉብኝት በሀገራቱ ታሪካዊ ግንኙነት አዲስ ምዕራፍ የከፈተ መሆኑን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር መለሰ ዓለም ገለጹ።

የሚኒስቴሩ ቃል አቀባይ አማባሳደር መለሰ ዓለም በሰጡት ሳምንታዊ መግለጫ ባለፉት አምስት ዓመታት ኢትዮጵያ በመካከለኛው ምስራቅና በባህረ ሰላጤው ያላትን ወዳጅነት ለማጠናከር በትኩረት መስራቷን ገልጸው ይህም ግንኙነቱን ከመጠራጠር ወደ መተባበር አሳድጎታል ብለዋል።

በኢትዮጵያ እና ተባበሩት አረብ ኤምሬቶች መካከል 17 ስምምነቶች ተፈራርመዋል ያሉት ቃል አቀባዩ አብዛኛው ኢኮኖሚያዊ ትብብርን የሚያሳድግ መሆኑን ገልጸዋል።

በሌላ በኩል ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በደቡብ አፍሪካ የብሪክስ ስብሰባ ላይ እየተሳተፉ መሆኑን የገለጹት አምባሳደር መለሰ ዓለም ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ ተቋማት ላይ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያላት መሆኑን አስታውሰዋል፡፡ በባለብዙ ወገን ዲፕለማሲ ረገድ ያላትን ድርሻ ለማሳደግ ይሰራልም ብለዋል።

ከመደበኛ ስብሰባው ጎን ለጎን የሁለትዮሽ ውይይት በትኩረት እንደሚሰራም ተመላክቷል።

አምባሳደር መለሰ ዓለም በ2016 በጀት ዓመት የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ሀገሪቱ ያላት ዲፕሎማሲ ግንኙነት ወደ ላቀ ደረጃ ለማሸጋገርና አጋርነትን ለማጠናከር ይሰራል ብለዋል።

በ2015 በጀት ዓመት በሰሜኑ ጦርነት ወቅት ከሀገራት ጋር የሻከረ የዲፕሎማሲ ግንኙነትን ወደነበረበት ለመመለስ ተሰርቷልም ነው ያሉት።

በ2016 ሀገሪቱ በዓለም አቀፍ መድረክ ተገቢውን ቦታ እንድታገኝ ትኩረት ተደርጎ ይሰራል ያሉት ቃል አቀባዩ የኢትዮጵያ የውጭ ግንኙነት ቅድሚያ ለጎረቤቶቻችን ይሰጣል፤ አካባባዊ ሰላም እንዲኖር ይሰራል ብለዋል።

በ2016 ወዳጅ ሀገራትን ለማብዛት በትኩረት እንደሚሰራ የጠቆሙት አምባሳደሩ ተደራሽ ባልሆነችባቸው አካባቢዎች ላይ ተደራሽ ለመሆን እንደሚሰራም አመላክተዋል።

በመስከረም ቸርነት