የተደረጉ የውጊያ ልምምዶች የሰራዊቱን የማድረግ አቅም ማሳደጉ ተገለጸ

የውጊያ ልምምዶች

ግንቦት 3/2014 (ዋልታ) በ6ኛ ዕዝ ባሉ ኮሮች የተደረጉ የውጊያ ልምምዶች የሰራዊቱን የማድረግ አቅም በከፍተኛ ደረጃ ማሳደጉ ተገለጸ።

በዕዙ ስር ያሉ ሁሉም ኮሮች ባለፉት ተከታታይ ወራት በአካል ብቃት፣ በተኩስ እና በተለያዩ የመሬት ገፆች ሲያካሔዱት የነበረውን የውጊያ ስልት ስልጠና አጠናቀዋል።

በየኮሩ የተደረጉ ወታደራዊ ስልጠናዎች ሰራዊቱ በቀጣይ የሚሰጡትን ግዳጆች በአስተማማኝ ለመወጣት የሚያስችሉ መሆናቸውም ተገልጿል።

በስልጠናው ማጠቃለያ ላይ የተገኙት የኮሩ ዋና አዛዥ ሜ/ጀኔራል አድማሱ ዓለሙ እንደተናገሩት ባሳለፍናቸው ወራቶች በየደረጃው ትኩረት ሰጥተን ያደረግናቸው እጅግ አድካሚ ስልጠናዎች የክፍለ ጦሮችን ወታደራዊ ዝግጁነት ወደ ላቀ ደረጃ ያሳድገዋል።

የኢትዮጵያን ኅልውና ማስጠበቅ እና የጠላቶችን ምኞት ማምከን የሚያስችል ወታደራዊ ልምምድ በየኮሮቹ የተደረገ መሆኑን የገለጹት ዋና አዛዡ እረፍት የለሽ ወታደራዊ ስልጠናዎችን በማካሄድ የማድረግ አቅምን በከፍተኛ ደረጃ ማሳደግ ተችሏል ብለዋል።

የክፍለ ጦር ምክትል አዛዥ ኮ/ል ቶሌራ ባቱ በበኩላቸው የተካሄዱት ወታደራዊ ልምምዶች በቀጣይ ሊሰጡ የሚችሉ ግዳጆችን የሚያቀሉ መሆናቸውን ገልጸው ሰራዊቱ ማንኛውንም ግዳጅ መፈፀም በሚችልበት የዝግጁነት ደረጃ ላይ ይገኛል ማለታቸውን ከመከላከያ ሰራዊት ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

ለፈጣን መረጃዎች፦
ፌስቡክ https://bit.ly/3Ma7QTW