“የተፃፈበትን የብር ኖት አትቀበሉ”በሚል እየተሰራጨ ያለው መረጃ መሠረተ ቢስ ነው-የኢትዮጵያ ብሄራዊ ባንክ

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ “የተፃፈበትን የብር ኖት አትቀበሉ” በሚል እየተሰረጨ ያለው መረጃ መሠረተ ቢስ መሆኑን ገለጸ።

ብሄራዊ ባንኩ ይህኑ እየተሰራጨ ያለ መረጃ በተመለከተ ዛሬ መግለጫ አውጥቷል።

ሙሉ መግለጫው የሚከተለው ነው።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ አዲስ የብር ኖት አሳትሞ ሥራ ላይ በማዋል ከመስከረም 6 ቀን 2013 ዓ.ም እስከ ታህሳስ 6 ቀን 2013 ዓ.ም በመላ አገሪቱ የብር ኖት ቅያሪ ሲያካሂድ ቆይቷል፡፡

ባንኩ መንግሥት ከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ ወጪ በማውጣት አዳዲስ የወረቀት ገንዘብ አሳትሞ ወደ ኢኮኖሚው ማስገባቱን ጠቅሶ የዚህን የወረቀት ገንዘብ አጠቃቀም በተመለከተም ጉዳት እንዳይደርስበት እና አላግባብ እንዳይከማች መመሪያ ማውጣቱን አውስቷል።

ሆን ተብሎ ወይም በቸልተኝነት በብር ኖት ላይ ጉዳት እንዳይደርስበት እንዲሁም ብዛት ያለው ገንዘብ ሕግን ባልተከተለ መልኩ ያለአግባብ እንዳይከማች ለማድረግ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ መመሪያ ቁጥር CMD/01/2020 ማውጣቱ ይታወሳል፡፡

በመሆኑም፣ የብር ኖቱ ረጅም ጊዜ እንዲያገለግል በማሰብ፦

1.በብር ኖቱ ላይ መፃፍ፣ መቅደድና በቀለም ማበላሸት፣ የትኛውንም ዓይነት ጉዳት ማድረስና ምልክቶቹን ያለፈቃድ ማባዛት የተከለከለና በሕግ የሚያስጠይቅ መሆኑን፣

  1. ለማስታወቂያ ሥራ ከተፈለገ ግን ለማባዛት የባንኩን ፈቃድ ማግኘት አስፈላጊ መሆኑን፣
  2. በጣም የተጎዱ የብር ኖቶች ሲያጋጥሙ ከዝውውር ስለሚወጡበት ሁኔታ ዝርዝር መመሪያ እየተዘጋጀ መሆኑን፣

4.ባንኩ መመሪያውን ወደ አማርኛ በማስተርጎምና በማብራራት ስለብር ኖት አጠቃቀም በየጊዜው ለህብረተሰቡ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራ የሚሠራ መሆኑን፣ እየገለፅን “የተፃፈበትን የብር ኖት አትቀበሉ” እየተባለ የሚናፈሰው ወሬ መሠረተ ቢስ መሆኑን ለመግለፅ እንወዳለን፡፡

 

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ

አዲስ አበባ

ታህሣሥ 28 ቀን 2013 ዓ.ም