የቲቢ በሽታ ልየታ፣ ምርመራና ህክምና ላይ በትኩረት መስራት ያስፈልጋል ተባለ

ዶ/ር ሊያ ታደሰ

ነሐሴ 19/2014 (ዋልታ) እ.ኤ.አ በ2030 የቲቢ በሽታን ለመግታት ቀጣይነት ባለው የልማት ግብ የተያዘው ዕቅድን ለማሳካት ተገቢውን ትኩረት ሳያገኝ የቆየው የህጻናትና አፍላ ወጣቶች የቲቢ በሽታ ልየታ፣ ምርመራና ህክምና ላይ ትኩረት በማድረግ መስራት እንደሚያስፈልግ የጤና ሚኒስትሯ ዶ/ር ሊያ ታደሰ ገለጹ፡፡

ሚኒስትሯ በሎሜ ቶጎ እየተካሄደ ባለው 72ኛው የአፍርካ አኅጉር የዓለም ጤና ድርጅት መድረክ ላይ በኢትዮጵያ በ2015 የጸደቀው የህጻናትና አፍላ ወጣቶች የቲቢ በሽታ ፍኖተ ካርታ ተግባራዊ መሆን ከጀመረ ወዲህ ህጻናትና አፍላ ወጣቶችን ከቲቢ በሽታ የመከላከልና ህክምና ሥራ መሻሻሉን ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ ከዓለም የቲቢ እንዲሁም ቲቢ-ኤች አይቪ ስርጭት ይበልጥ ከተስፋፋባቸው 30 አገራት አንዷ መሆኗን ያወሱት ዶ/ር ሊያ ታደሰ የቲቢ በሽታን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የሚሰሩ ሥራዎች ለቲቢ ይበልጥ ተጋላጭ የሆኑና የተዘነጉ የኅብረተሰብ ክፍሎች ላይ ትኩረት ማድረግ ይገባል ብለዋል።

እ.ኤ.አ በ2030 የቲቢ በሽታን ለመግታት ቀጣይነት ባለዉ የልማት ግብ የተያዘወን ዐቅድ ለማሳካት በተለይም ከሰሃራ በታች ያሉና በቲቢ በሽታ ስርጭት ይበልጥ እየተጎዱ ያሉ እገራት ላይ ትኩረት መስጠትና ማገዝ እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡

ሁለንተናዊ የጤና ሽፋንን ለማረጋገጥ የተያዘውን የዓለም ጤና አጀንዳ ከግብ ለማድረስ ፍትሃዊነትን ማረጋገጥ ወሳኝ ነው ያሉት ሚኒስትሯ በአጠቃላይ የጤና አገልግሎት ፍትሃዊ ተደራሸነትን በማረጋገጥ ለህጻናትና አፍላ ወጣቶች ትኩረት በመስጠት ከቲቢ በሽታ መከላከልና ሁለንተናዊ ጤንነታቸው እንዲጠበቅ ማድረግ አይነተኛ ምሳሌ መሆኑን ተናግረዋል፡፡