የታለመ የነዳጅ ድጎማ ተጠቃሚ ተሽከርካሪዎች መለያ ስቲከር ይፋ ሆነ

ግንቦት 28/2014 (ዋልታ) የሕዝብ ትራንስፖርት አገልግሎት ሰጪ ተሽከርካሪዎች የታለመ የነዳጅ ድጎማ ተጠቃሚ መሆናቸውን የሚገልፅ መለያ ይፋ ሆነ፡፡

የትራንስፖርትና ሎጅስቲክ ሚኒስቴር እንደገለጸው መለያው ሁለት አይነት ሲሆን ለመደበኛ ሀገር አቋራጭ የሕዝብ ትራንስፖርት ተሽከርካሪዎች እና በክልል ለሚገኙ ተሽከርካሪዎች የሚያገለግል ነው፡፡

መለያው ተሽከርካሪዎቹ የታለመ የነዳጅ ድጎማ ተጠቃሚ መሆናቸውን ለነዳጅ ማደያዎችና ለሚመለከታቸው ሌሎች አካላት መረጃ የሚሠጥ ነው ተብሏል፡፡

ሙሉ ሰማያዊ ቀለም ያለው መለያ ለሀገር አቋራጭ የሕዝብ ትራንስፖርት ተሽከርካሪዎች የሚያገለግል ሲሆን በነጭ መደብ የተዘጋጀው መለያ ደግሞ በክልል ለሚገኙ የሕዝብ ትራንስፖርት አገልግሎት ሰጪ ተሸከርካሪዎች የሚያገለግል ነው፡፡

በቅርቡ ተግባራዊ ለመሆን በዝግጅት ላይ የሚገኘው የታለመ የነዳጅ ድጎማ ሥርዓት ተጠቃሚ የሚሆኑ የሕዝብ ትራንስፖርት አገልግሎት ተሽከርካሪዎችን የመለየትና መረጃ የማጥራት ሥራ እየተከናወነበት እንደሚገኝ ይታወቃል።